Sunday, November 25, 2012

ከአይበሰብሴው ከረጢት ወደ ዘንቢል- ዘንበል


(ጌታቸው አሰፋ፤ ነሐሴ 5  ቀን  2004 ዓ.ም.) በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ በቅርቡ የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀምን የሚከለክል ህግ ወጣና መነጋገሪያ ሆነ - በጥቅሙና ጉዳቱ ዙሪያ።  ይህ ከመሆኑ ከአምስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ስስ ፌስታሎችን የሚከለክል ህግ አወጣች። በየካቲት 5 1999 በነጋሪት ጋዜጣ ላይ በወጣውና አዋጅ ቁጥር 513/1999 ተብሎ በሚታወቀው ይህ ‘የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ’ አንቀጽ ስምንት ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 3 ላይ የፕላስቲክ ከረጢቶች በተመለከተ እንዲህ ይላል፤
1) በባለሥልጣኑ(አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን) በሚወጣ መመሪያ ከሚወሰነው ቀን ጀምሮ በስብሶ ወደ አፈር የሚደባለቅ መሆን አለመሆኑን የሚያሳይ ምልክት ያልተደረገበትን የፕላስቲክ ከረጢት ለገበያ ማቅረብ የተከለከለ ነው።
2) ውፍረቱ 0.03 ሚሊ ሜትር እና ከ0.03 ሚሊ ሜትር በታችም ሆኖ በስብሶ ከአፈር ጋር የማይዋሃድ የፕላስቲክ ከረጢት የማምረት ወይም ወደ ሃገር ውስጥ የማስገባት ፈቃድ መስጠት የተከለከለ ነው።
3) የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /2/ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለሥልጣኑ ውፍረቱ 0.03 ሚሊ ሜትር እና ከ0.03 ሚሊ ሜትር የሚያንስ ሆኖ በስብሶ ከአፈር ጋር የማይዋሃድ የፕላስቲክ ከረጢትን ተለይቶ ለተገለፀ አገልግሎት ብቻ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ ወይም በአገር ውስጥ እንዲመረት የሚወስን መመሪያ ያወጣል ።
እነሱና እኛ
የፕላስቲክ ከረጢቶች ባደጉት አገሮች የሚከለከሉበት ምክንያትና በእኛ አገር ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ የሚፈለጉበት ምክንያት ክብደት ለየቅል ነው። ቶሮንቶም ሆነች ሌሎች አቻ ከተሞች የቆሻሻ መጠናቸውን በመቀነስ ለቆሻሻው መቅበሪያ የሚያስፈልጋቸው የመሬት ስፋት(ውድ ነው) ለመቀነስና ብሎም ተያይዞ የሚመጣው የከተማው ቆሻሻ ማስወገጃ ወጪ ለመቀነስ ስለሚጠቅማቸው ነው። ከዚህ አልፎ በስብሰው ከአፈር ጋር የማይዋሃዱትና አንዴ ብቻ ጥቅም ላይ ውለው የሚጣሉት የፕላስቲክ ውጤቶች የሚመረቱት የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትሉ የፔትሮልየም ውጤቶች በመሆኑ እነዚህም ከማስወገድ አንጻርም የሚከለክሉ አሉ።
በአገራችን ግን በተለይ  በተለምዶ ስስ ፌስታል ብለን የምንጠራው ውፍረቱ 0.03 ሚሊ ሜትር እና ከ0.03 ሚሊ ሜትር  በታች የሆነው የፕላስቲክ ከረጢት መዘዙ ሰፊ ነው። ሲጀመር እኛም አገር ቢሆን እነዚህ የፕላስቲክ ከረጢቶች አንድ ጊዜ ብቻ ነው ጥቅም ላይ የሚውሉት።  ቆሻሻን (እነዚህ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ጨምሮ) በተገቢው ቦታና ሁኔታ በመጣል፤ በመሰብሰብና በማስወገድ ፈንታ ስስ ፌስታልም የትም ይጣላል። ምንም ስስ ቢሆኑ አሁንም እነዚህ ስስ ፌስታሎች የተሰሩት ያው ከፔትሮልየም ውጤቶች በመሆኑ የትም በሚጣሉበት ወቅት በስብሰው ከአፈሩ ጋር አይዋሃዱም። በአገራችን የትም የመጣሉና መበስበስ ያለመቻሉ ጉዳይ በከተማም በገጠርም መዘዙ ከፍተኛ ነው።  በየከተሞቻችን በየመንገዱ በየቦዩ በየሰፈሩና በየአደባባዩ የሚጣለው ፌስታል በየከተማው ውበት ላይ የተደነቀረ እንከን ነው። ከዚህ የሚብሰው ግን ፌስታሎቹ ውሃና ሌላ ፍሳሽ በማቆር ለበሽታ አምጪና አስተላላፊ ነፍሳት የማራቢያ ማዕከል ሆነው ማገልገላቸው ነው። ይህ እንግዲህ ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉ ከውሃና ፍሳሽ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱና እስከሞት ድረስ በሚያደርሱ ሕመሞች የሚሰቃየው ሰው ቁጥር በርካታ በሆነባቸው ከተሞቻችን  ከነዚህ ፌስታሎች ጋር በተያያዘ የከተሜው አበሳ እንዲጨምር የሚያደርግ  ነው።
ይህ የከተማ ጣጣ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነበትና የውሃና ፍሳሽ አገልግሎትም በሌለበት የአገሪቱ የገጠር ክፍልም ችግሩ ያው፤ መዘዙ ግን ከፍ ያለ ነው። በገጠር ከጤና ጉዳይ በተጨማሪ ሌሎች ተጣይ-ፌስታል-በቀል ጠንቆች አሉ። ገጠሬው በነጻ ወይም በሳንቲም ስባሪ የሚያገኘውን ስስ ፌስታል የትም (በማሳም ከማሳም ውጪ) ሲጥለው ከማሳ ውጪ የተጣለውም በነፋስ አድራሽነት አድራሻው ማሳ ላይ ይሆንና አይበሰብሴው ፕላስቲክ ቀስ በቀስ በስስ የአፈር ንጣፍ ይሸፈናል። ማሳው ታርሶ ቢዘራበትምና ቢያበቅልም (ለዛውም ከበቀለ) ቡቃያው አስፈላጊውን ንጥረ ነገር አግኝቶ ስር ሰዶ እንዳያድግና እንዳያፈራ በአጭሩ እንዲቀጭ ያደርገዋል። እነዚህ ስስ ፌስታሎች የሚጣሉት ዓመቱን ሙሉ ነው ፤ አርሶ አደሩ ማሳውን የሚያርሰው ግን በዓመት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ(በልግ አብቃይ ቦታዎች ላይ) በመሆኑ  እነዚህ ፌስታሎች ከማሳው ጋር በቀላሉ ያለ ምንም ከልካይ የመገናኘት እድላቸው ሰፊ ነው። በቀላል አመክንዮ መሰረት ብዙ ስስ ፌስታሎች በየማሳው በተጣሉ ቁጥር ብዙ ቡቃያዎች ለፍሬ ሳይበቁ እንዲቀሩ ይሆናል። የማሳው ስፋት ከጊዜ ወደጊዜ እየጠበበ ለሚመጣበት አርሶ አደር የእያንዳንዷ ቡቃያ ማፍራት ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል። ሌላው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ፌስታል-በቀል ጠንቅ የሚያያዘው  ከከብቶች ጋር ነው። ስስ ፕላስቲኮቹ በነፋስ ተወስደውም ሆነ ተጥለው በየሳሩና በየግጦሹ ሲገኙ ከብቶቹ ደግሞ ሳር እንግጣለን ብለው አብረው ስስ ፕላስቲኩን ይወጣሉ። ፕላስቲኩ ጉሮሮአቸው ላይ ሲቀረቀር አፍኖ ይገድላቸዋል። ‘አያ በሬ ሆይ አያ በሬ ሆይ ሳሩ አየህና ገደሉን ሳታይ?’ የሚለውን የቆየ ይትብሃል ‘አያ በሬ ሆይ አያ በሬ ሆይ ሳሩ አየህና ፕላስቲክ በላህ ወይ?’ በሚለው መተካት ስህተት ላይሆን ይችላል - ገደልም ፕላስቲክም እንደ ገደል መግደል እስከጀመረ ድረስ። ይህ ንድፈ ሃሳባዊ ትንተና ሳይሆን በሬዎቻቸው በስስ ፌስታሎች ታፍነው የሞቱባቸው አርሶ አደሮች በየቦታው አሉ። የአንድ አርሶ አደር አንድ በሬ ሞተ ማለት ደግሞ አንድ የመድን ዋስትና የሌለው ትራክተር ተቃጠለ ማለት ነው። ከጥጃነት አሳድጎ ወይም ገዝቶ ለአቅመ-በሬነት ካበቃ በኋላ በሞት ሲያጣው ከጥጃነት አሳድጎ ወይም የሌለውን ገንዘብ አውጥቶ በመግዛት በአንዴ የሚተካው አይደለምና።
ድኅረ አዋጅ
እንግዲህ ከላይ በተጠቀሱት ከተማዊና ገጠራዊ ምክንያቶች መነሻነት ነው መንግሥት በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በኩል በሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅራቢነት ከዛም በፓርላማ ያሳወጀው። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ስስ ፌስታሎች በአዋጁ መሰረት እንዳይገቡ ተደርጓል። ስስ ፌስታሎች ግን አሁንም በአገሪቱ አሉ - ምክንያት በአገር ውስጥ የሚመረተው ስላልተቋረጠ።
አዋጁና አዋጁን ተከትሎ የሚመጣው የተለያየ ቅርጽ ሊኖረው የሚችለው ቅጣት ብቻውን ሙሉ በሙሉ ይሰራል ተብሎ ስለማይገመት የመፍትሔው ቀሪ አካል ሌላ ቦታ መፈለግ አለበት።  ለዚህም አማራጭ ከረጢቶች እንዲመረቱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አንዱ ነው - የመንግሥት ድጋፍ የሚያሻው ነገር። ተጠቃሚዎችም ትኩረታችን ከአይበሰብሴው ወደ ዘንቢል ዘንበል ማድረግ አለብን።  ዘንቢል ወደ መጠቀም መመለስ ዘርፈ ብዙ ረቦች አሉት። እያንዳንዱ ዘንቢል በየቤቱ በአገልግሎት ላይ የሚቆይበት እድሜ ሲታይ ስንትና ስንት ስስ ፌስታሎችን ከማስቀረት አንጻር ያለው ከፍተኛ ጠቀሜታ ማየት ይቻላል - ለፍሬ የሚበቃው ቡቃያ፤ ከሞት የሚተርፈው በሬና ሌላ የቤት እንስሳ፤ ቁጥራቸውና ጉዳታቸው የሚቀንሰው ውሃና ፍሳሽ ወለድ ሕመሞች እና የመሳሰሉት።
ምን ይህ ብቻ!... ስስ ፌስታሉ ከውጪ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ሲመረት ዋነኛ ጥሬ እቃዎቹ ከውጪ የሚገቡ ከመሆናቸው አኳያ እንደ አገር የውጪ ምንዛሪ ያስወጡናል። በተቃራኒው ዘንቢል የሚሰራባቸው ጥንታዊያኑ ጥሬ እቃዎች አገር በቀል በአብዛኛው የእጽዋት ውጤቶች  አልፎ አልፎም ከቆዳ ውጤቶች ሲሆኑ በስብሰው ከአፈር ጋር መዋሃድ የሚችሉ ናቸው። ‘ዘመናዊው’ የዘንቢል መስሪያም ከአሮጌ ነገር ለምሳሌ አሮጌ ፕላስቲክ ነክ ጆንያዎች ወይም ጥቅም ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ገመዶችን ያካተተ ነው። ይህም ከውጪ ምንዛሪ አኳያም ሆነ መላልሶ ከመጠቀም አንጻር ያለው ረብ ስስ ፌስታሎችን ያስከነዳል።
ከማኅበራዊ  ጥቅም አንጻርም ብናየው ዘንቢል የሚሰራው ዝቅተኛ ገቢ በሚኖራቸው ግን ብዙ ቤተሰቦችን በሚያስተዳድሩ በርካታ የዕደ ጥበብ ሰዎች በመሆኑ ለበርካቶች ገቢን ከማስገኘት አንጻር ጥቅሙ ከፍተኛ ነው።
ስለዚህ መንግሥት በአንድ በኩል የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስችል አማራጭን ከማበረታት ጋር ተዛዝሎ የሚመጣ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል። ወደ ሱቅ ወይም ገበያ ስንሄድ ‘ስስ ፌስታልን ወዲያ ዘንቢልን ወዲህ!’ የሚል ልማድም ማስፋፋት ያስፈልጋል - በተጠቃሚዎች ዘንድ።ሩዋንዳን ማየት ይሄኔ ነው! ይ(ያ)ቆየን። 
 =======


አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: