Sunday, November 25, 2012

ፍሰትና ብክነት


(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥቅምት 9  ቀን  2004 ዓ.ም.) በአንድ አገር አዛላቂ የምጣኔ ሀብታዊ ክንውንውታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ፍሰቶች አሉ። እዚህ ውስጥ የምናካትታቸው የቁስ፤ የመረጃ፤ የኃይል፤ የገንዘብ እንዲሁም የእንስሳት የእጽዋትና የሰው ፍ(ል)ሰት ናቸው። እነዚህን ፍሰቶች በተገቢው መጠን ቦታና ጊዜ መጠቀም ስንችል ነው በምጣኔ ሀብታችን ላይ የሚኖራቸው በጎ ተጽእኖ ማጉላት የሚቻለው። አለበለዚያ ብክነት ይከተላል። እስቲ አንድ በአንድ እንያቸው።

የቁስ ፍሰት
በዚህ ስር የሚካተቱት የጠጣር፤ የፈሳሽና የጋዝ ፍሰቶች ናቸው። ከውጪም ይሁን ከአገር ውስጥ ወደ ኢኮኖሚው የሚቀላቀሉት ቁሶች ማን ማን ይባላሉ? በስንት መጠን የት ነው ያሉት? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ምጣኔ ሀብታዊና አካባቢያዊ ፋይዳ አለው። ጥሬ እቃዎች ወይም ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ከውጪ አገር በምን ያህል መጠን ገብተው በምን ያህል መጠን ጥቅም ላይ እንደዋሉ ማወቅ ከብክነት አኳያ ያለብንን ችግር አይነትና ስፋት ለማወቅ ይረዳል። በሌላ በኩል የተለያዩ የምርት ምንጮችንና የምርት ጠቀሜታዎችን አጥንቶ የተሻለውን ለመምረጥ እድል ይሰጣል። ይህ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ነው። ከአካባቢያዊ ፋይዳ አንጻር ደግሞ ከምርት ጋር ተዋህደው ወደ ኢኮኖሚው የሚገቡት ኬሚካሎች በተለይ ለጤና ጠንቅ የሆኑቱ ከምንጫቸው እስከ መጨረሻቸው የትነታቸው መታወቁ ከመከላከል እስከ ማከም ያለውን ስራ አሳልጦ ለመስራት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህ አሰራር በቀጥታ ጤና አዋኪ ለሆኑ ውህዶች ብቻ ሳይሆን አካባቢን በመበከል ለሚጀምሩትም የሚሆን ነው። ሲጀመር ኬሚካሎች በተፈጥሮ የሚገኙም ሰው ሰራሽ የሆኑም አሉ። ሁለቱም አይነት ኬሚካሎች በካይም ጎጂም የሚሆኑት በዋናነት በሁለት ምክንያቶች ነው - በአነስተኛ መጠንም ቢሆን መገኘት የሌለባቸው የአካባቢ ክፍል ውስጥ ሲገኙ እና ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቅ ወይም ለወትሮው ቢገኙም ምንም አይደለም ተብሎ በሚታሰብበት ክፍለ-አካባቢም ቢሆን ከመጠን በላይ ሲገኙ። ለዚህም ነው የቁጥጥር አይናችን የትኞቹ፤ የት፤ በምን ያህል መጠን እንዳሉ ማየት የሚችል መሆን የሚገባው።  ከበርካታ ዓመታት በፊት በጸረ ተባይነትም ለሌላም ጥቅም ተብለው ወደ አገራችን የገቡት ኬሚካሎች መጠን ምን ያህል ነበር? የት ነው ያሉት? ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቀሩት ምን ያህል መጠን አላቸው? የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኆቻችንን የተቀላቀሉት ምን ያህል ናቸው? በየሰዉ አካል ውስጥ ያሉትስ ምን ያህል ይሆኑ? በጡት ወተት በኩል ከእናት ወደ ልጅ የተላለፈው ኬሚካል መጠንስ? እነዚህ ሁሉ መልስ ማግኘት አለባቸው - ምንም ቢከብዱም።
የኃይል ፍሰት
በውኃ ኃይልም አሁን አሁን ደግሞ በነፋስ ኃይል ጭምር አገራችን የክፍለ-አህጉራችን የኃይል ገንዳ መሆን የምትችልበት መንገድ እየተጠረገ ነው። ያለን የማመንጨት ኃይል ከፍተኛ መሆኑ በጎ ነው። የምናመነጨው ኃይል እየጨመረ የሚሄድ መሆኑም ደስ ይላል።  እንደዛም ሆኖ ግን ‘አሁን ያለውም ወደፊት የሚጨመረውም የኃይል ፍሰት መጠን ምን ይመስላል?’ የሚለውን አቢይ ጥያቄ አንዴ ብቻ ሳይሆን በተከታታይነት የሚመልስ አሰራር መዘርጋት ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ አለው።
ከምንጠቀምበት ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞም ይሁን ከአሰራር ጉድለታችን ጋር በተቆራኘ በየማሰራጫ መስመሩ የሚባክነው የኃይል መጠን ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ፤ በየቤታችን አሁንም ከምንጠቀምባቸው ኃይል-በዪ እቃዎች (አምፖሎቻችንን ጨምሮ) አባካኝነትና ከአጠቃቀም ጉድለት ጋር በተያያዘ
ብን ብትን ብሎ የሚቀረው የኃይል መጠን ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማወቅና ብክነቱን ቢያንስ ለመቀነስ መቻል ከቤት እስከ አገር የሚተርፍ ረብ አለው።

የእንስሳት የእጽዋትና የሰው ፍ(ል)ሰት
በዚህ ጽሑፍ ሁሉም እንስሳት እና እጽዋት ለማዳዎች ናቸው። በተለምዶ ለማዳና የዱር ብለን የምንጠራቸው ከሰው ጋር ባላቸውና በሌላቸው ግንኙነት ላይ ተመስርተን ሲሆን በዚህ ጽሁፍ እሳቤ ግን ለማዳነታቸው ከመጀመሪያ ቄያቸው ጋር ባላቸው ቁርኝት መሰረት ነው። እንደየተፈጥሮ ባህሪያቸው በጠባብም በሰፊም ቦታ በመዟዟርም በመቀመጥም ኑሯቸውን የሚገፉ እንስሳት ዘገዳም እንስሳት ዘቤት አሉ።  የትኛው እንስሳ በምን ያህል ቁጥር በየትኛው ቦታ ወይም በምን አይነት መልክአ ምድር አለን? ነበረን? በምን ሁኔታና መቼ ቁጥሩ ጨመረ ወይም ቀነሰ? መጨመራቸውም መቀነሳቸውም ተፈላጊም የማይፈለግም ሊሆን ይችላል- እንደ እንስሳው እንደ ቦታው እንደጊዜው። የቁጥርና የአይነት ለውጡ እንደሁኔታው ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል። ወይም ቢያንስ የጥሩም የመጥፎም ምልክት ሊሆን ይችላል። እጽዋትም እንደዚሁ መገኘት ያለባቸው ቦታና ጊዜ አለ - በአይነትም በብዛትም። የሁለቱም አድራሻ፤ የቤተሰብ ብዛት፤ እድሜ ካወቅን የፍ(ል)ሰት መኖርና አለመኖር ብቻ ሳይሆን በጎም ክፉም አንድምታውን መለየት እንችላለን። ለይተን ስናበቃም እንደአስፈላጊነቱ አትጊም አራሚም ስልቶች ቀይሰን ወደ መተግበር ለመሸጋገር ይቻለናል። በተመሳሳይ ሁኔታ ገጠሬም ከተሜም የሆነው ሰው ሳይፈልግ ተገዶ ወይም ፈቅዶ ወዶ ቀዬውን ለቆ ሊፈልስ ይችላል። ሲፈልስ ከኋላ የሚተዋቸው ጠባሳዎች እንዳሉ ሁሉ የሚያድናቸውም የሚቆሰቁሳቸውም ቁስሎች ይኖራሉ። ወደኋላ ሄደንም፤ አሁን ያለውንም ሆነ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን የተፈዋሽና የተቆስቋሽ ቁስሎች ብዛትና ስፋት ለማወቅ የሚቻለው ሲጀመር ‘ስንት ሰው የት በምን ሁኔታ ነበረን፤ አለን፤ ይኖረናል?’ ብለን ስናውቅና ‘ምን ሳቢ ማግኔቶች ምን ገፊ ነፋሶች አሉ?’ ብለን ስናጤን ነው።   
የገንዘብ ፍሰት
አገራችን ያላት የገንዘብ መጠን የውሱን ውሱን ነው። ‘ምን ያህል ገንዘብ፤ የትና ለምን ጥቅም ዋለ?’ ‘የተሻለው አጠቃቀምስ የትኛው ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ባለ ትልቅ አንድምታ ናቸው- በአገራችን ለአገራችን። ከላይ ያየናቸው ሦስት አይነት ፍ(ል)ሰቶች በአግባቡ ከተያዙ ገንዘብ የሚያስገኙና የሚቆጥቡ በተቃራኒው ከሄዱ ደግሞ ቀዳዳ ኪሶች ሆነው የመቀጠል እዳላቸው ሰፊ የሆኑ ናቸው። ውጤታማ የሙስና መከላከልም ሆነ የመቆጣጠሪያ ስልት፤ ስሉጥ የግብር መሰብሰቢያ ስርዓት ወዘተ ሊኖረን የሚችለው  ኢኮኖሚው ውስጥ ህይወት ዘርቶ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ፍሰት ጤናማ ካልሆነው ፍሰት መለየት የሚችሉ፤ ፍሰቶችን ጥርት አድርገው የሚያሳዩን የመስተዋት መፍሰሻዎች ሲኖሩን ነው።
የመረጃ ፍሰት
‘የመረጃ አገሩ የት ነው?’ ‘በተለይ ጥራቱስ?’ እነዚህ የቢልዮን ብር ጥያቄዎች ናቸው። ቀደም ብለን ያየናቸው ፍሰቶች በሙሉ በተመለከተ ኃላፊውን፤ የአሁንም ሆነ መጻኢውን ለመተንተን፤ ስልት ቀይሶ ለማስተካከልና ማትጊያ መንገዶች ለመጥረግ መሰረቱም፤ ግድግዳውም ጣራውም መረጃ ነው። መረጃ ሲባል በቁጥር የሚጠራ፤ ሊደመር፤ ሊባዛ፤ ሊካፈል፤ ሊቀነስ የሚችል ለንጽጽር፤ ለክትትልና ለቁጥጥር የሚመችና በአግባቡና በጥራት የተሰነደ መረጃ ማለት ነው። መረጃ ግን እንዲሁ ከሆነ ቦታ ድንገት ዱብ ሊል አይችልም። በገበያዊ እይታ የሁሉ ነገር ማንቀሳቀሻ ሞተር የፍላጎትና አቅርቦት ምጣኔ ነው - የአንድ ምርት ውድነትና ርካሽነት የሚወስነውም ያው ይህ ሞተር ነው። በሌላ በኩል ለአንድ ነገር ያለው ፍላጎት ከፍ ሲል አቅርቦቱም እንዲጨምር ያደርጋል። በተቃራኒው ፍላጎት ሲቀንስ አቅርቦቱም እንዲሁ ይቀንሳል።  ለመረጃም ቢሆን ከፍ ያለ ፍላጎት ሲኖር አቅርቦቱም ከፍ ያለ ይሆናል። አቅራቢው ክፍል መረጃ ተጠቃሚ ለሆነው ክፍል በስፋትና በጥራት ለማቅረብ ጥቅማዊ ግዴታ የሚሰማው ተጠቃሚው በስፋት፤ በጥራት፤ በፍጥነትና በተከታታይነት ለሚቀርብ መረጃ ዋጋ መስጠት ሲችል ነው። መረጃ-ጠገብም መረጃ-አልባም ነገሮች ያለምንም ልዩነት በሚበላና በሚጠጣ ህብረተሰብ መካከል አንጀት-አርስ መረጃ በቀላሉ አይገኝም። ብክነት ምንም ይሁን ምን አይመረጥም። ይሁንና የብክነቶች ብክነት የመረጃ ብክነት ነው። እያንዳንዱ የሚባክን መረጃ ያለንበት ሁኔታ እንዳናውቅና የድንብርብር ህይወት እንድንገፋ ያደርገናል -እንደ አገር። በመጨረሻ - ባለፈው ዓመት በደርባን ደቡብ አፍሪካ ተደርጎ የነበረው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤና ድርድር ቀጣዩ የሚካሄደው በዶሃ ኳታር በመጪው ወር ነው። ይህ አምድም ለቅድመ-ጉባኤ፤ ለጊዜ-ጉባኤና ለድህረ-ጉባኤ ትንተና እያሟሟቀ ይገኛል። በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በዶሃው ጉባኤ አፍሪካን በመወከል የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን  ሚና ተክተው ለመጫወት ዝግጅት መጀመራቸው ተሰምቷል። እንመለስበታለን።
 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: