Sunday, November 25, 2012

‘አረንጓዴ’ አብዮት


(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥቅምት 2  ቀን  2004 ዓ.ም.) ዓለማችን ከፓለቲካዊ አብዮቶች (መነሻ ቃል፡ አበየ - ‘እምቢ አለ’) በተጨማሪ ሌሎች ዘመን ቀያሪ፤ ሂደት ለዋጭ አብዮቶችን  አስተናግዳለች - የግብርና አብዮት ፤ የኢንዱስትሪ አብዮት ፤ የሳይንስ አብዮት፤ የዲጂታል አብዮት። እነዚህ አብዮቶች ‘አብዮት’ ያሰኛቸው ከዛ በፊት ግብርና ወይም ኢንዱስትሪ ወይም ሳይንስ ወይም ዲጂታላዊ እንቅስቃሴ ወይም ስራ ስላልነበረ አይደለም። በመጠናቸውና በአይነታቸው ከተለመደውና ከነበረው አሰራርና አካሄድ ለየት ባለ መልኩ ሁኔታ ቀያሪ በሆነ መገለጫ ግብርናው፤ ኢንዱስትሪው፤ ሳይንሱና የመረጃ ቴክኖሎጂው ስለተስፋፋና አገሮች ከተለመደው መንገድ ‘በእምቢታ’ ወጥተው ወደ አዲሱ መንገድ ስለገቡ ነው ከአብዮት ጋር ተያይዞ የሚነገርላቸው።
የግብርና አብዮት
ከአንድ ሄክታር ይገኝ የነበረውን የምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደግ ጋር በተያያዘ የተገኘውን የለውጥ እምርታ የግብርና አብዮት እንለዋለን።  የግብርና አብዮት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተለያየ ወቅት ተካሄዷል። ለምሳሌ በእንግሊዝ ከአስራ አምስተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ለአራት ክፍለዘመናት ከኢንዱስትሪ አብዮትና ከሳይንስ አብዮት ጋር መነሻና መድረሻ እየሆነ ተከስቷል።  በአረቡ ዓለምም ከዚህ በጣም ቀድም ብሎ ከስምንተኛው ክፍለዘመን እስከ አስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ አብዮት ነበር።  በንጽጽር በቅርቡ በኤዥያና (በተለይ በህንድ) በላቲን አሜሪካ (በዋናነት በሜክሲኮ) የተካሄዱትን የግብርና አብዮቶች ነው አረንጓዴ አብዮት ተብለው የሚጠሩት።በ1960ዎቹ 1970ዎቹ በህንድና ሜክሲኮ የተከሰተውን አረንጓዴ አብዮት እውን እንዲሆን የደገፉ የሮክፌለር ፋውንዴሽን ፤ የፎርድ ፋውንዴሽን እንዲሁም የዓለም ባንክ ነበሩ። እነዚህ ድርጅቶች ይህን አረንጓዴ አብዮት በ1980ዎቹ በአፍሪካም እንዲከሰት ሊያደርጉ ሲሞክሩ የዓለም አቀፍ አካባቢ ተቆርቋሪዎች ተቃውሞ በማሰማታቸው ይህን ድጋፍ ለመስጠት አልፈቀዱም። የተቃውሞው ምንጭ በነዚህ አብዮቶች ተጠቃሚ ለምርት መጨመሩ ግብአት የሚሆኑትን ነግሮች የሚያቀርቡት የምዕራብ አገሮች ትልልቅ ኩባንያዎች ናቸው እንጂ ገበሬው አይደለም የሚል ነው። ጉዳቱ በአካባቢም በዘላቂ ምርታማነትም በኩል ከፍተኛ ነው የሚል ነው።
ይህ ከሆነ ሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ካለፈ በኋላ እነሆ አፍሪካ በተቃውሞው ምክንያት የዘገየው አረንጓዴ አብዮት መፈንጃ  ልትሆን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ሲጀመር ‘አረንጓዴ አብዮት’ የሚለው ስም አሳሳች ነው። ‘ለምን?’ ቢባል ለምሳሌ ይህ ስም ‘አረንጓዴ ኢኮኖሚ’ ከሚለው ጋር ዝምድና የሌለውና አረንጓዴነቱ ከአካባቢ ተጽእኖ አለመኖር ወይም አነስተኛ መሆን ጋር የማይገናኝ ነው። የስም አወጣጡም አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ንግግር ሲያደርጉ “በነህንድና ሜክሲኮ የተካሄደው አብዮት በሶቭዮት ህብረት የነበረውን ቀይ አብዮት ያይደለ፤ የአረቦች አይነት ነጭ አብዮት ያይደለ አብዮት ነው። ይህን አብዮት አረንጓዴ አብዮት ብየዋለሁ” ያሉትን መነሻ በማድረግ ነው።
የአፍሪካው አብዮት
ከዛን ጊዜ ጀምሮ የግብርና ምርት መጠን ላይ ከፍተኛ እምርታ ማምጣት ‘አረንጓዴ አብዮት’ ተብሎ ከመጠራቱ አኳያ ነው አፍሪካ ማካሄድ አለባት የሚባለው የራሷ የግብርና አብዮትም ‘የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት’ የሚል ስያሜ ያገኘው። ይህ የአፍሪካ አብዮት እውን እንዲሆንም የአፍሪካ መንግሥታት ጥረት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እና እንዲሁም የታወቁ ግለሰቦችና ባለጸጎች እንቅስቃሴ እየታየ ነው። ከአዲሱ የአፍሪካ አረንጓዴ የግብርና አብዮት ጀርባ የተከበሩ ሰዎች አሉ- ኮፊ አናን እና ቢል ጌትስ የመሳሰሉት። እነዚህ ስዎች የሚሰሩትን የሚያውቁ ናቸውና በገንዘብ ብዛትም ይደለላሉ ብዬ አላስብም። ይሁንና እነሱንና እነሱ ሚና የሚጫወቱበት የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት መድረክ መጠቀሚያ ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ ኩባንያዎች ይኖራሉ እና የኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በቅርቡ በታንዛኒያ አሩሻ ከተማ የአፍሪካ አረንጓዴ የግብርና አብዮት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ መድረክ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድኅን ተሸላሚ ነበሩ(ይመቻቸው!)። ሽልማቱ የያራ ሽልማት ተብሎ የሚታወቅ በኖርዌይ ኩባንያ የሚዘጋጅ ሲሆን ሽልማቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰባት ዓመታት በፊት ሲጀመር ተሸላሚ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙትን የሽልማት ገንዘብ ለሴት ተማሪዎች ስኮላርሺፕ እንዲሆን ያዋሉት ነበር።
የአገራችን ደጋማው ክፍል ለዘመናት በመታረሱ ምክንያት በሄክታር የሚገኘው ምርት በጣም አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ አዲስ መሬት ወደ ግብርናው እስካልተቀላቀለ ድረስ በቂ ምርት ማግኘት ከባድ ከሆነ ቆይቷል። በየጊዜው ደግሞ ሊጨመር የሚችል አዲስ መሬት ሊኖር አይችልም። በመሆኑም ካለው መሬት የምናገኘውን ምርት መጨመር የምንችልበት መንገድ መፈለግ የግድ ነው።  መንግሥት በግብርና ኤክስቴንሽን ባደረገው ጥረት አበራታች ውጤትም ተገኝቷል። ለምርት መጨመር ምክንያት የሆነው ማዳበሪያን ከውጪ በውጪ ምንዛሪ በማስገባት በመሆኑ ውሎ አድሮ አቅሙ ከተገኘ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ማዳበሪያም ሆነ ሌላው የግብርና ግብአት በአገር ውስጥ ማምረት የምንችልበትን እድል መጠቀም ወሳኝ ነበር። በዚህ አቅጣጫ ሜታል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሊሰራቸው ያሰባቸውን ፋብሪካዎች በዋናነት የዩሪያና የዳፕ ማዳበሪያዎችን ለማምረት የሚያስችሉን ናቸው። በቅርቡ የኮርፓሬሽኑ ዋና ኃላፊ ብርጋዴዬር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከእጽዋት የሚሰራው ማዳበሪያም እንደሚካተት ማሳወቃቸው የሚበረታታ ነው።
ሁለንተናዊ ግምገማ
በተጀመረው መጠነ ሰፊ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ብዙ ሳንገፋ እንደ አገር ማድረግ ያለብን ነገር አለ። ‘ምን ያህል መሬት? በምን ያህል መጠን? ለምን ያህል ጊዜ ነው በግብአቶች ጣራ ስር ማዋል ያለብን? ይህን ስናደርግ የሚፈጠሩ የጎንዮሽ ተጽእኖዎች እንዴት ነው የምንመክታቸው? የግብአቶች ምርጥ የአጠቃቀም ባህልስ የምንፈጥረው እንዴት ነው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች በሁለንተናዊ ግምገማ ስልት የየዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መመለስ አለባቸው።
በዚህ በኩል የህንድ ልምድ በበጎም በመጥፎም ጥሩ መነሻ ሊሆነን ይችላል። ‘ህንድ ራሷን መመገብ አትችልም። ከአሁን በኋላ ካላት የህዝብ ብዛት አንጻር መጪው ጊዜ ለህንድ መጥፎ ነው።’ ተብሎ በተተነበየ በስድስት ዓመት ውስጥ እድሜ በዋናነት ሩዝ ላይ መሰረት ላደረገ አረንጓዴው አብዮት ራሷን ከመመገብ አልፋም በስፋት ወደ ውጪ ለመላክ በቅታለች። ይህ በጎው ነው።  በመጥፎ ጎኑ ደግሞ መጠነ ሰፊና ያልተመረጠ የማዳበሪያና የጸረ ተባይ አጠቃቀም ጋር የሚያያዝ የአረንጓዴ አብዮት ሰርቶ ማሳያ የሆነችው የህንዷ ፑንጃብ ግዛት የታየው እየጨመረ የመጣ የበሽታና (ለምሳሌ ከጸረ ተባይ ጋር የተያያዘ ካንሰር) የአካባቢ ተጽእኖ (የክርሰ ምድር ውኃ ብክለት እና የመሳሰሉት) በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። ሌላው ከምርጥ ዘሩ አይነት ጋር የሚያያዝ የጎንዮሽ ጠንቅ አለ። በሩዝም ሆነ በስንዴ ላይ የተደረገው የምርት ጭማሪ እምርታ የተከሰተው በግንዱ ላይ ይውል የነበረው መዋዕለ ህይወት  ፍሰት ተቀንሶ ፍሬ መጨመር ላይ እንዲውል በማድረግ ድንክዬ ስንዴና ድንክዬ ሩዝ ግን ከመደበኛው ዝርያ የበለጠ የሚያፈሩ እንዲሁን በማድረግ ነው። ይሁንና ይህ ዘዴ ከምርት ሂደት በኋላ ከፍሬው በተጨማሪ ለሌላም አገልግሎት (ለምሳሌ ለከብት መኖ) የሚውለው አጠቃላይ የቃርሚያ መጠን የሚቀንስ ነው። ይህ ደግሞ እኛን በመሳሰሉ አገሮች ከጠቅላላ የቃርሚያ መጠኑ ያገኙት የነበረው ጥቅም ያሳንስብናል። በዛ ላይ ደግሞ እነዚህ ምርጥ ዘሮች ከፍተኛ የማዳበሪያ፤ የውኃ እና የጸረ ተባይ ግብአት የሚጠይቁ ናቸው። እንዲያውም በቂ ግብአት ካላገኙ ከመደበኛ ዘሮች ያነሰ ምርት ነው የሚሰጡት። ይህ ጉዳት ነው።
በእርዳታ እህል ተወልዶ፤ በእርዳታ እህል አድጎ፤ በእርዳታ እህል ተድሮ የሚኖር የህብረተሰብ  ክፍል ይዘን(ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ድህነታችን በተመለከተ ለከፍተኛ የመንግሥትና የፓርቲ አመራሮች ከተናገሩት) የማሳዎቻችንን ምርት የሚጨምር አቅጣጫ በፓለቲካም ይሁን በሌላ ምክንያት በመቃወም አገራችን በምግብ ራሷን የምትችልበትን ቀን ማራዘም የለብንም።
እንደዛም ሆኖ ግን ‘የተመረጠውና አዛላቂ የሆነው መንገድ የትኛው ነው?’ ብለን የአጭሩንና የረጅሙን ዘመን ተግዳሮቶችንና ጸጋዎችን ለማጣጣም ከአሁኑ ማሰብና ማሰላሰል ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን በአገራችን አሁን ያሉት በጎ ጅምሮች ባለ-ብዙ ዘርፍ አብዮት የማምጣት እድላቸውን ሰፊ ማድረግ እንችላለን።   
=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: