Sunday, November 25, 2012

ግብርናችን


(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥቅምት 16  ቀን  2004 ዓ.ም.) በአጼ ኃይለሥላሴ ትተዳደር የነበረችው ኢትዮጵያ ሀያ ሰባት ሚልዮን ህዝብ ነበራት።  ከሃያ አንድ ዓመታት የዙምባቤ ቆይታ በኋላም ባለቤታቸውን ‘ጓድ ውባንቺ ቢሻው፤’ ብለው የሚጠሩት መንግሥቱ ኃይለማርያም የአገሪቱ ርእሰ ብሄር የነበሩ ጊዜና ኢሰፓን በመሰርቱበት ዓመት አካባቢ  ደግሞ ኢትዮጵያዊያን አርባ ሚልዮን ገደማ ነበርን። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተረከቧት አገር ደግሞ ቢያንስ ሰማንያ ሚልዮን ሰዎችን ይዛለች።

ምግብና ተመጋቢዎች 
ከድሮ ጋር ሲነጻጸር የገጠር ኗሪው ሕዝብ ብዛት ጨምሯል። የከተሜውም እንዲሁ። በአጠቃላይ የተመጋቢው ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል። የምግቡ መጠንስ?
ከአስራ ዘጠኝ አምሳ ዓመተ ምህረት ጀምሮ ከአስር በላይ የግብርናን ምርት መጨመረን እንደ ግብ ያካተቱ እቅዶች በየወቅቱ በነበሩት መንግሥታት ተነድፈው ነበር።
የምርት ጭማሪን በሦስት መልኩ ማየት ይቻላል። በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚመረተው ምርት ጠቅላላ መጠን አንዱ መለኪያ ነው። ይህ መለኪያ ወደ እርሻ የሚቀላቀል አዳዲስ መሬት ወደ ስራ በማስገባት ሊጨምር ይችላል። ከዚህ የተሻለ የሚሆነው በሄክታር የሚመረተው ምርት መጠን እየጨመረ ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ መለኪያ ነው። አጠቃላይ የምናመርተው መጠን ለጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ቁጥራችን ተካፍሎ የሚገኘው የምርት መጠን በነፍስ ወከፍ ደረጃ ማየት ደግሞ ከሁሉም የተሻለ መለኪያ ነው። ምክንያቱም የምርት እድገት የሚጨምርበት ፍጥነት የሕዝብ ቁጥር ጋር ካልተጣጣመ በአንድ ማዕድ ዙሪያ ያሉ የአፎች ቁጥር ከጉርሻዎች ቁጥር ሲበልጥ የሚሆነው ያህል እድገቱን ረብ-የለሽ ያደረገዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሄክታር ይመረት የነበረው የሰብል መጠን እየጨመረ ነው። ስንዴ በሄክታር ከአርባ ኩንታል ወደ አምሳ ኩንታል በአማካይ እንዲሁም እስከ ሰማንያ እና ዘጠና ኩንታል ድረስ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች እንዳሉ ተሰምቷል። በአጠቃላይ ሲሰላም በአማካይ ጭማሪ እንዳሳየ ማየት ይቻላል። በነፍስ ወከፍ ሲሰላ ግን አሁንም በጉልህ የሚታይ ጭማሪ አያሳይም ባለፉት አርባ ዓመታት። የምግቡ መጠን ቢጨምርም  የተመጋቢው ቁጥርም በዛው መጠን ስለጨመረ ይህ ስሌት ከፍ ሊል አልቻለም። እርግጥ በሰው ሀብት አቅምና ፍላጎት ዙሪያ በማዕከላዊ እስታስቲክስ ኤጀንሲ በተካሄደው ጥናት  ላይ የተመሰረተ መረጃ ስንመለከት በአገራችን በ1983 ዓ.ም አንዲት እናት በአማካይ 6 ነጥብ 4 ልጆች ትወልድ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የምትወልዳቸው ልጆች ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 8 ዝቅ ብሏል። የአማካይ ነገር - የልጆች ቁጥር ሳይቀር በነጥብ ነው የሚያስቀምጠው! - መቼስ ምን ይደረግ። ለማንኛውም ይህ አማካይ የሚነግረን ነገር ቢኖር ለምሳሌ አስር እናቶች ባሉበት ሰፈር የተመጋቢው ቁጥር በድሮው አካሄድ ቢኬድ ሊሆን ይችል ከነበረው አንጻር በአስራ ስድስት ሰዎች ማነሱን ነው። በአገራችን ሃያ ሚልዮን እናቶች ቢኖሩ ብለን ብናሰላ ደግሞ ይኸው የቀነሰው ብዛት ወደ ሰላሳ ሁለት ሚልዮን ይደርሳል ማለት ነው።
ስለዚህ አሁንም ከእያንዳንዱ ሄክታር ማግኘት የምንችለውን ያህል ምርት ወደ ማግኘት የሚወስደን አዋጪ መንገድ ሁሉ መጠቀም አለብን። ‘አዋጪ’ የሚለውን ለማስካት ደግሞ ለዘለቂታው ከረጅም ጊዜ አኳያ እየጨመረ የሚመጣ የምርት መጠን በሚያሳፍሰን መልኩ ነው ግብርናችን መደራጀት ያለበት።
ባንክና በጀት
ለግብርናው ዘርፍ መሰረት ከሆነው የአፈርና የውኃ ሀብታችን ውስጥ መጠበቅ የሚገባንና እየጠበቅን ማከም የሚገባንን ደግሞ እያከምን የሚንሄድበት መንገድ ማበጀት አለብን። በስፋት መሰራት ያለበት ይህ የጥበቃና የሕክምና ስራ ከጅምሩ የተሳካ እንዲሆን ደግሞ ለተመጋጋቢ ስራዎች የቅድሚያ ትኩረት መስጠት ይጠይቃል።
አፈራችን ለሰብሎች፤ ለዛፎችና ለሌሎች ተክሎች እድገትና ምርታማነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነግሮች ማከማቻ የባንክ ሂሳብ አድርገን ማየት አለብን። ከባንክ ሂሳቦች አዋጪው የሚወልደው  አይነት እንደሆነው ሁሉ ጥሩ ወለድ ለማግኘት ደግሞ መጀመሪያ የሚቀመጠው ገንዘብ፤ በየጊዜው የሚገባውና የወለዱ መጠን ወሳኞች ናቸው።  ከነዚህ በተጨማሪም አስቀማጩ ከተቀማጩ ገንዘብ በብዛትና ቶሎ ቶሎ የሚያወጣ ከሆነ የሚያገኘው ወለድ ትንሽ እንዲሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ገንዘቡ በጠቅላላ ለረጅም ጊዜ ሳይቆይ ቶሎ እንዲያልቅ ያደርገዋል። ይህ የገንዘብ ቁጠባ ስርአት አሰራር ለአፈር ሀብታችንም የሚሰራ ነው። በዋናነት በተፈጥሮ ማዳበሪያና በአጋዥነት ደግሞ በዘመናዊ ማዳበሪያ ወደ ማሳው የሚገባው አዳባሪ ንጥረ ነገር በረጅም ጊዜ የአፈሩን ለምነት ከመጠበቅ አኳያ ልናስተዳድረው ይገባል።
በከርሰ ምድርም በገጸ ምድርም ያለው የውኃ ባንካችንም ገቢና ወጪውን ከጊዜ ርዝመትና ከዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አንጻር ልናስተዳድረው ያስፈልጋል። በየምርት ወቅቱ የምንጠቀመው የውኃ መጠን አስቀድሞ መበጀት ወሳኝ ነው። ልክ የገንዘብ በጀት ከግብር ይህን ያህል፤ ከልማት ድርጅቶች ይህን ያህል ገንዘብ ቢገኝ እንዲሁም ከእርዳታና ከብድር ደግሞ ይህን ያህል ቢመጣ ተብሎ እንደሰራው ሁሉ የውኃ በጀትም ከገጸ ምድር ውኃ ይህን ያህል፤ ከከርሰ ምድር ውኃ ይህን ያህል አለን፤ ይህን ያህል ዝናብ ደግሞ በዚህ ቦታና ጊዜ ከጣለ  ይህን ያህል ብለን መበጀት አለብን። በገንዘብ በጀቱ ላይ እርዳታውና ብድሩ የተፈለገው ያህል ባይሆንስ የሚለው ታሳቢ እንደሚደረገው ሁሉ በውኃውም ዝናቡ የምንጠብቀው ያህል ባይሆንስ በሚል መሰላት አለበት።
በውኃ ባንክ ሂሳባችን ውስጥ ታሳቢ ከተደረጉት ክምችቶች መካከል እያነሰና እያሽቆለቆለ የሚመጣ ካለ በአጭርና በረጅም ጊዜ ክምችቱ ከፍ የሚልበትን መንገድ ወደ መፈለግ እንሄዳለን ማለት ነው።  እዚህ ላይ በመንግሥት ደረጃ ለውጭ ምንዛሪ ክምችታችን የሚሰጠው ትኩረት ግማሹን ያህል መስጠት ብቻ ሊበቃ ይችላል።
የምርምርና ስርጸት ተቋሞቻችን ሚና በየቦታው ያለው የውኃ መጋዘን እና የአፈር አልሚ ነገሮች ይዘትን የሚያስጨምሩና የሚቀነሱ አካባቢያዊ ምክንያቶችን አጥንቶ ከነመፍትሄው በማቅረብ ተግባራዊ ስራ እንዲሰራ ማገዝ  ይሆናል።
ትስስር
ስኬታማ ግብርና ከሌሎች ዘርፎ ጋር ማስተሳሰርን ይጠይቃል።የእርሻ/ግብርና ምርምር ጣቢያዎቻችን ከድሮም ጀምሮ የተለያዩ ምርምሮችን ከማካሄድ አልቦዙንም።
በኢዜአ በየጊዜው የዜና ሽፋን ከሚያገኙት ነገሮች መካከል እነዚህ የምርምር ጣቢያዎች ያስገኟቸው የተሻሉ ዝርያዎች ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው። የምርምር ውጤቶችን ወደ መስክ ወስዶ አስፈላጊ የሆነ መጠነ-ሰፊ ለውጥ ከማምጣት አኳያ ግን ብዙ ይቀረናል - እንደ አገር።  
ገበያ የሁሉም ነገር መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ቢታወቅም አምራች ትክክለኛ ዋጋ የሚያስገኝለት ገበያ ወሳኝ ነው። የምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጨምሯል። በትክክለኛ መንገድ ለአምራቹ የሚደርሰው ድርሻ ግን አሁንም ተመጣጣኝ  አይደለም። ለአምራች ተገቢውን ዋጋ የማያስገኝ ምርት ማምረት በነፍስ ወከፍ አርሶ አደርም ሆነ በአገር ደረጃ ጎጂ ነው። በአንድ የምርት ወቅት የተገኘው ምርት ከወጣበት ወጪ ያነሰ ዋጋ ካስገኘ በሚቀጥለው የምርት ዘመን ለማምረት ስለማያበረታታ ብቻ ሳይሆን የማምረቻ ወጪውም ስለማይቻል በቀጣይነት በቂ ምርት እንዳይኖር ያደርጋል - የምግብ እጥረት እንዲከሰትም ምክንያት ይሆናል። የዶ/ር እሌኒ የአእምሮ ልጅ የሆነው የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ድርጅት ሲቋቋም እንዲህ አይነት አላስፈላጊ ክስተትን ለማስወገድ ታስቦ ነው። ከተመሰረተበት ጊዜ አኳያ ጥሩና ተስፋ ሰጪ ውጤትም እያስገኘ ነው። ከዚህ በላይ ሄደን የግብርናው ምርቶቻችን ባለ ተጨማሪ እሴት እንዲሆኑ ለማድረግ ግብርናው ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር የበለጠ መቆራኘት አለበት። ለምርት ገበያው ጅማሮ ጥሩነት አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል የመረጃ መረብ አውታር መዘርጋት፤ የመንገዶች አንጻራዊ መሻሻል ይገኙበታል። አሁንም እነዚህ ዘርፎች በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ከተሰሩ ምርታማነትን በነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ደረጃ ሲሰላም እምርታ እንዲያሳይ የሚያግዙ ይሆናሉ።
እነዚህን ስራዎች በውጤታማነት በማስኬድ በኩል የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።  በሚቀጥሉት ዓመታት አጠቃላይ የምናመነጨው ኃይል በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ እየተሰራ ነው። የኃይል አቅርቦታችን በዋናነት ከውኃ ሆኖ እየቀጠለም የነፋስና የጸሐይ ኃይል ማመንጫዎች ቀስ በቀስ የማይናቅ ድርሻ እየያዙ እንዲመጡ ለማድረግ የሚሰራው ስራ መልካም ነው። አዳዲስ የኃይል አቅርቦት ስራዎቻችን ግብርናውን ከማዘመን አኳያ ሊቃኙ ያስፈልጋል።

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: