Sunday, November 25, 2012

‘አዲስ አበባን ያጸዳ የጸዳ ዋጋ ከአምላኩ’


(ጌታቸው አሰፋ፤ ሐምሌ 28  ቀን  2004 ዓ.ም.)ሰኔ ላይ አንስተነው ወደነበረው የአዲስ አበባ ጽዳት ጉዳይ ተመልሰን መጥተናል። የጽዳት ስራውን የሚፈጽም፤ ክትትል ለሚያደርግ፤ የተሻሉና አዳዲስ አዛላቂ ሃሳቦች የሚያፈልቅ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ነው እንግዲ አብያተ እምነት የሚመጡት - የተከታዮቻቸውን የጊዜ፤ የጉልበት፤ የእውቀትና የገንዘብ ሀብት ይዘው። አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት አብያተ እምነት ቁጥራቸው በርካታ ነው። አነሰም በዛም በየቤተ እምነቱ በመደበኛነት የሚገለገለው ተከታይ ቁጥር ጠቅላላ ድምር ቀላል አይደለም - ኢመደበኛውን ሳንቆጥር።

ጽዱና ውብ ሸገርን ለመፍጠር ረዘም ያለ ጊዜ መስጠት ያለባቸው ይኖራሉ። ከስንት አንዴ ለአጭር ጊዜ መጥተው ጉልበታቸውን ማፍሰስ ያለባቸው ሰዎችም መኖር አለባቸው። የጊዜውም የጉልበቱም አስተዋጽኦ ለማበርከት የማይሳካላቸው ከእውቀታቸውና ከገንዘባቸው ለቀቅ ቢያደርጉ ቢሉ ተፈላጊ ነው።  የአዲስ አበባ ሰፈሮች፤ አደባባዮች፤ ዋና መንገዶችና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዲሁም የየአጥሩ ጥጋ ጥግ በጽዳት እንዲጠበቁና በአረንጓዴ ሽፋን እንዲዋቡ ተከታታይ ስራ ቢሰራባቸው አዲስ አበባ በአጭር ጊዜና በዘላቂነት ጽዱና ውብ መሆኗ አይቀርም። በየቦታው የሚገኙ አብያተ እምነት በተወሰነ ርቀት የሚገኘውን ቦታ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው።
ለምሳሌ  ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን ያለበት ቦታ እንደ እምብርት ይዘን በየአቅጣጫው በእግር እስከ ሰላሳ ደቂቃ የሚያስኬዱ ርቀቶች ብንሄድ የተለያዩ አብያተ እምነት እናገኛለን።  ቦሌ መድኃኔዓለም፤ራሱ ቅዱስ ኡራኤል፤ ቅዱስ እስጢፋኖስ፤ ካዛንቺስ ያለው የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙበት ማለት ነው። አንድ ሁለት መስጊዶችም አሉ - አንድ ካዛንቺስ አካባቢ፤ አንድ ደግሞ ወደ ሰላሳ ስድስት ቀበሌ መናፈሻ አካባቢ።  እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ሌሎች የፕሮቴስታንት ቸርቾችም ላይጠፉ ይችላል። ስለዚህ ቦሌ መድኃኔዓለም ከቦሌ ድልድይ እስከ አትላስ ሆቴል አካባቢ ያለውን ዋና መንገድና የሰፈር ውስጥ መንደር እንዲሁም ሁለቱን አደባባዮች ቢያጸዳ፤ ቢያስውብና ቢንከባከብ። ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያንም ወደ ታች እስከ አትላስ ሆቴል መዳረሻ ያለው የቀበና ድልድይ ይይዛል። በተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት - እስከ ካዛንቺስ ቶታል ያለው በአንድ በኩል እንዲሁም እስከ ባምቢስ  በሌላ በኩል እንዲሁም እስከ ዘሪሁን ህንጻ በሌላኛው ይሆናል ማለት ነው። በቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን ስር ያሉ ምእመናንና ሰንበት ተማሪዎች ወዘተ ሁለት ድልድዮች ያሉበት በአራት አቅጣጫ የሚገኙ በቆሻሻ፤ በሽንትና በእንከኖች የተሞሉ መንገዶችንና አካባቢዎች ጽዱ  አደረጉ ማለት ነው። የእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንንም እንደዛው ማየት ይቻላል። በመርካቶ አካባቢም በቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያንና በአንዋር መስጊድ አስተባባሪነት ሊጸዳና ሊዋብ የሚችለው የቦታ ስፋት ማሰብ ይቻላል።
በእያንዳንዱ አብያተ እምነት ውስጥና ዙሪያ የተደራጁ ማኅበራትም አሉ። እነዚህ መንፈሳዊም ማኅበራዊም ማኅበራት አባላቶቻቸውን ለምሳሌ በማስተባበርና በመከታተል ስራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ አስተዋጽኦ ጥቅም አለው።  በእርግጥ ማን ምን ይስራ የሚለው በተለያዩ መንገዶች የሚቀመር ነው።
አብያተ እምነት ከላይ የተዘረዘረውን ማድረግ ያለባቸው ማንም ሳያስገድዳቸው ነው። ከማዕከላዊ ኃላፊዎቻቸው ወይም መስሪያ ቤቶቻቸው ጥሪ ሳይፈልጋቸው ወይም ቢሮክራሲያዊ አካሄድ መከተልሳይጠበቅባቸው  መሆን ይገባዋል። ጋዜጣዊ መግለጫ ወደ መስጠት ሳይቸኩሉ፤ የሚታይ፤ የሚዳሰስና የሚ(ማይ)ሸተት ለውጥ የሚያመጣ ስራ ላይ ብቻ በማተኮር የሚሰሩት መሆን አለበት።
ይህ አሰራርና ሀሳብ አዲስና ልዩ ላይሆን ይችላል። ከአሁን በፊት በሌሎች ጠባብ ቦታዎች የተሞከረና የተጀመረም ሊሆን ይችላል። እንደዛ መሆኑ ደግሞ ጥቅም አለው። በቀጥታ አዲስ አበባን ወይም ሌላ የኢትዮጵያ ከተማን ጽዱ ከማድረግና ከማስዋብ አኳያ ያለን ውስን ልምድም ቢሆን ተቀምሮ መጠቀም ያስፈልጋል። በተጨማሪ በቀጥታ ከቆሻሻ ጋር ባይያዙም እኳን ከአደረጃጀትና አሰራር ጋር የሚገናኙ ልምዶችን መመልከት ተገቢ ይሆናል። እዚህ ላይ መጠቀስ የሚችል ልምድ አለ - በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን አካባቢ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለው የወጣቶች የጥምቀት በዓል አከባበር ዝግጅት። እነዚህ ወጣቶች ማንም ሳያደራጃቸው፤ ማንም ሳያስገድዳቸውና ማንም ሳይደጉማቸው በራሳቸው ተነሳሽነት በአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያን ዙሪያ ከሚገኙ ሰፈሮች በመሰባሰብ አስፈላጊውን ወጪ አውጥተው ታቦታተ ህጉ የሚያልፉባቸውን መንገዶች በሙሉ ልቅም አድርገው አጽድተውና በምንጣፍ አስውበው በዓሉ ደማቅና ያማረ እንዲሁን እያደረጉ ነው።  እነዚህን ወጣቶች ለዚህ ስራ ያነሳሳቸው የተለያየ ምክንያት ሊኖር ቢችልም ዋናው ግን እምነታቸው ነው - በስራው አስፈላጊነት ማመናቸው። ወጣቶቹ ሰው ላመነበት ነገር ሲሰራ ምን ድረስ መሄድና መስራት እንደሚችል የሚያሳዩ አርአያዎች ናቸው።
በተመሳሳይ ሁኔታ አብያተ እምነት ተከታዮቻቸው በየዙሪያቸው ያለውን መንገድና ሰፈር በጽዳትና በውበት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዲሸከሙ ለማድረግ የማሳመን ስራ መስራት ይገባቸዋል።
የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም የአብያተ እምነቱና የሌሎች የጠቀስናቸው አካላት ስራን በመደገፍና ከምር በማቀናጀት ሚናውን መጫወት አለበት። መሬት ላይ ከምናየው መንግሥት ማቀናጀት የሚገባው ግን የማያቀናጀው ተራ የሚመስል ግን የገንዘብ ኪሳራው ከፍተኛ የሆነ ጉዳይ ነው ‘ከምር ‘የሚለውን አስፈላጊ የሚያደርገው።  ለምን እዚህ ላይ በምሳሌነት አናነሳውም? አንድ ሰፈር ላይ ወይም ዋናም ሆነ ኢ-ዋና መንገድ ላይ በቴሌ፤ በውሃ ስራዎችና በመብራት ኃይል የሚሰሩ ስራዎችን በመካከላቸውና ከመንገድ ስራዎች ጋር በመሆን በመቀናጀት ለመስራት ስለማይነጋገሩና ስለማይናበቡ መንገድ ስራዎች የሰራው መንገድ ገና ጥቅም ላይ ከመዋሉ ቴሌ መጥቶ ይቆፍረዋል፤ ከቴሌ ቢተርፍ ከውኃ ሥራዎች ወይም ከመብራት ኃይል አንዳቸው እንዳልነበረ ያደርጉታል። ብዙ ጊዜ ተቆፍሮ ሲያበቃ እንደነበረ ተመሳሳይ የአስፋልት ንጣፍ ሳይደረግለት ጠባሳ እንደሆነ ይቀራል። አንዱ ከቆፈረው በኋላ መንገድ ስራዎች እንደገና ቢሰራው እንኳን ሌላው መጥቶ ይቆፍረዋል። መንገድ ስራዎች ደግሞ በተቆፈረ ቁጥር እየመጣ እንዲሰራ መጠበቅ አያዋጣም። ሲጀመር እነ ውኃ ስራዎችና ቴሌ እንዲሁም መብራት ኃይል መንገዱ ውድ በሆነ የአስፋልት ስራ ከመነጠፉ በፊት ስራቸውን ሰርተው የማይጨርሱበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም - - - ነበር።
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ‘ከየቦታው የሚሰበሰበው ቆሻሻ የት ይሂድ?’ የሚለው ጥያቄም መመለስ አለበት። የዚህ ጽሑፍ ዋና ማጠንጠኛ ባይሆንም ቢያንስ አንድ ሁለት ነገሮችን ልበል። ቆሻሻው 1)ካርቦናዊ ፤ 2)ሕይወት ዘዳግም ያላቸው፤ 3)ተቃጣይ፤እና 4)‘ቀሪ’ በሚባሉ ክፍልፋዮች መሰረት ከምንጩ መለየት አለበት። እዚህ ላይ ‘አርጩሜና ካሮት’ የግድ ይላል። በተቻለ መጠን የሚደፋው ‘ቀሪ’ ክፍልፋይ መጠን መቀነስ አለበት። ከምንጭ የመለየት ስራ በአግባቡ የማይፈጽሙ (ለምሳሌ ‘ሰፈሮች’) የሆነ ቅጣት ቢጤ መክፈል አለባቸው - የአርጩሜ ምሳሌ።  ጥሩ ጥሩ ስራዎችን ወደፊት የሚያስኬድ ካሮትም ያስፈልጋል። ለምሳሌ ካርቦናዊ የቆሻሻ ክፍልፋዮችን ባዮጋዝና ኮምፖስት ማምረት ወደሚችሉ የማምረቻ መስመሮች የሚያስገቡ እንዲሁም ለሕይወት ዘዳግም ብቁ የሆኑ ክፍልፋዮችን ወደመልሶ መጠቀሚያ ጣቢያ የሚያመጡ ሰፈሮች ከሚገኘው የገንዘብ ጥቅም ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ፤ ሽንት-ጠገብ ጥጋጥጎችን እንደገና መልሰው ለሚያቋቋሙ ደግሞ ልዩ ማበረታቻ።
ከምንጭ የመለየት ስራውን ለማሳካት ቋቶቹ ለየክፍልፋዩ አይነት ተለይተው የተቀመጡ፤ ያለችግር የሚታወቁና በቀላሉ የሚጋቡ ሆነው መሰራት አለባቸው።  ያሉት ቋቶች ባሉበት ማሻሻል የማይቻል ከሆነ ቋቶቹን ወደ ማቅለጫዎች ወስዶ ለሌላ አገልግሎት አውሎ በምትካቸው ሌሎች ማራኪ ቋቶች በስራ ላይ ማዋል ይገባል።
እያንዳንዱ አብያተ እምነት በሚሸፍናቸው ቦታዎች ውስጥ የሚገኙትን ቋቶች በሰኔው እትም ላይ እንዳነሳነው አይነት አሰራር ዘርግቶ የማስተዳደር ኃላፊነት ይወስዳል ማለት ነው።  አዲስ አበባን ሰፈር በሰፈር ጽዱ አድርጎና አስውቦ ለማስቀጠል የሚያስፈልገው የአንድ ጊዜና ቀጣይ ወጪ ተሰልቶ በሁለቱም ጽሑፎች ለተጠቀሱት ባለድርሻዎች (የንግድ ተቋማት፤ ኩባንያዎችና መስሪያ ቤቶች እንዲሁም አብያተ እምነት) መከፋፈል አለበት።
ስራው ሳይቆም እንዲቀጥል ለማድረግ ያልተወሳሰበና ያልተንዛዛ ኢ-ማዕከላዊ ተቋማዊ ቅርጽ ወሳኝ ነው። ‘አዲስ አበባን ያጸዳ የጸዳ ዋጋ ከአምላኩ ያገኛል።’ - አብያተ እምነት የአስተምህሮአቸው አካል ቢያደረጉትስ?
 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: