Sunday, November 25, 2012

ስለጅምላ በጅምላ ለጅምላ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ጳጉሜን 3  ቀን  2004 ዓ.ም.) አዲስ አበባ በጣም ሰፍታለች። በርካታ መንገዶች ተሰርተዋል እየተሰሩም ነው - በማሳለጫዎችና በመሽሎኪያዎች እንዲሁም በመንገደ-ብዙ ድልድዮች እየተደገፉ ነው። የመኪኖች ቁጥርም እንዲሁ። የመጓጓዣ ችግር ግን አሁንም እንዳለ ነው። በቁጥርና በጥራት የሚገለጽ። በተለየ በተወሰኑ መስመሮችና ጊዜያት። የየራሳቸውም ሆነ የየመስሪያቤታቸው መኪኖች ከሚያሽከረክረውና  በአንጻራዊነት ጥቂት ከሚባለው የአዲስ አባባ ነዋሪ ውጪ ያለው ሰው ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ራሱንና ቁሱን ለማጓጓዝ የሚጠቀመው በጅምላ መጓጓዣዎች ነው። የጅምላ መጓጓዣ ውስጥ ውይይት ታክሲዎች፤ ሚኒ ባስ ታክሲዎች፤ ከኮንትራት ውጪ የሚሰሩ ትንንሽ ታክሲዎች፤ ሎንቺናዎች፤ የአንበሳ አውቶብሶችና የሃይገር አውቶብሶች ይካተታሉ። በቅርቡ በአዲስ አበባ ስራው የተጀመረው የቀላል ባቡር መጓጓዣም የዚህ ክፍል ዋና አካል ነው።
 የጅምላ መጓጓዣዎች በሌላ አጠራር የህዝብ መጓጓዣዎች እንላቸዋለን። በአጠቃላይ አስቀድሞ በኮንትራትና በተመሳሳይ አሰራር ባልተመቻቸ ሁኔታ የማይተዋወቁ ሰዎች መጓጓዝ የሚችሉባቸውና መንገድ ላይም ይሁን ሀዲድ ላይ የሚሽከረከሩ ተሽከርካሪዎች ሁሉ የጅምላ መጓጓዣዎች ናቸው።
የጅምላ መጓጓዣ መጠቀም እንደ ከተማ፤እንደ አገር እንዲሁም እንደ ግለሰብም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።
ሁሉም የአዲስ አበባ ኗሪ በግለሰብ ወይም በቤተሰብ ደረጃ መኪና ይጠቀም ወይም ይኑረው ብንል (አይችልም ግን ይችላል እንኳን ብንል) አዲስ አበባን ከማጨናነቅ፤ አየሩን በጣም ከመበከልና እንዲሁም አገሪቱ ከውጪ በውጪ ምንዛሪ የምታስገባው ነዳጅ ላይ ጫና ከመፍጠር አንጻር መዘዙ ከፍተኛ ነው።
በአዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ያሉት መንገዶችና ወደፊት መገንባት የሚችሉት መንገዶች ላይ መንቀሳቀስ የሚችሉት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ያለ ገደብ ሊያድግ አይችልም- አይገባምም። የከተማው የአየር ብክለት ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰበት ነው። ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃዎች የማይበጁና የማይወሰዱ ከሆነም በእጅጉ እየተባባሰ የመሄዱ ጉዳይ የግድ ሊሆን ነው። ኢትዮጵያ የራሷ ነዳጅ ፍለጋ ላይ ከተሰማራች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። በፍለጋው ላይ የተሰማሩት ኩባንያዎች ብዛትና አይነትም ከጊዜ ወደጊዜ እየበዛ መጥቷል - አንድም ጠብታ እስካሁን ባናገኝም።  የራሷ የሆነ ብዙ ነገር ያላት አገራችን የራሷ ነዳጅና የራሷ ወደብ እንዲኖራት የማይመኝ የማይናፍቅ የለም። ከታች ነዳጅ ከላይ ወደብ እስክታገኝ ድረስ ግን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ የምታስገባውን ነዳጅ በአግባቡና በቆጣቢ አሰራር መጠቀም አለብን - እንደ አገር እንደ ህዝብ። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የጅምላ መጓጓዣዎች ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት። በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው ማጓጓዝ ከመቻላቸው አኳያ በአገልግሎት ሲሰላ የሚወስዱት ነዳጅ እያንዳንዱ ሰው በነጠላ ወይም በአነስተኛ ቁጥር ከሚጓጓዝባቸው መኪኖች የተሻለ ነው። የሚሻሉበት መጠን በአንድ ጊዜ መያዝ ከሚችሉት ሰው ብዛት ጋር የሚያያዝ ነው። ከግል መኪና ፤ ውይይት ወይም ሚኒባስ ታክሲዎች ይሻላሉ። ከዛም ሎንቺናዎች፤ ሃይገሮችና መደበኛ አንበሳ አውቶብሶች። ከዛም በበለጠ በቅርቡ በሜታል ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ተገጥመው በአዲስ አበባ መንገዶች መምዘግዘግ የጀመሩት ‘ፍሬው ኃይሉ’ አውቶብሶች ብዙ ሰው በትንሽ ነዳጅ በማጓጓዝ ይሻላሉ። ከሁሉም የሚሰቅለው ግን የከተማ ቀላል ባቡር ነው - ሲጀመር ነዳጅ ሳይሆን በአገራችን ከውኃችን በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሚዘወር።  የዚህ ጽሁፍ ዋና መልእክት “በበቂ ምክንያት ካልተገደዳችሁ በስተቀር በመኪና አትሂዱ። በሃይገርና በአንበሳ አውቶብስ ሂዱ።” የሚል ነው። የዚህ ምክር ቢጤ መልእክት ችግር ደግሞ ሊሰማው የሚችለው ሰው ከጥቂት እስከ ዜር  መሆኖ ነው -  አይገኝም እንጂ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ ሁሉም ሰው በመኪና እንጂ በሕዝብ አውቶብስ መሄድን አይመርጥምና። የዚህ አይነት መልእክት አይሰ’ሜነት የጅምላ መጓጓዣ በተለያየ ምክንያት ገና ያላደገባት አገራችን ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም።  በሁለንተናዊ መልኩ የበለጸጉና ላላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ‘የለውም’ ለሚባለው የኅብረተሰብ ክፍልም በአገልግሎት አቅርቦት በመድረስ ከተሳካላቸው በርካታ ያልሆኑ አገሮች ውጪ የጅምላ መጓጓዣ መጠቀምን የሚያበረታታ ስርአት በብዙ አገሮች በስፋት የሚገኝ አይደለም። ከጃፓን ሌላ በዚህ ረገድ የተሳካላቸው አገሮች ከሞላ ጎደል የሚገኙት በአውሮፓ በተለይም በሰሜን አውሮፓ ነው። ለአስራ አንድ ዓመታት በኖርኩበት ስዊድን ውስጥ መኪና ነድቼ አላውቅም ብቻ ሳይሆን መንጃ ፈቃድም አልነበረኝም (እርግጥ መጨረሻ አካባቢ ላወጣ ብልም እየወደቅኩ ተቸግሬ ነበር) - አመቺ የሆነ የህዝብ ማመላለሻ ስርዓት ስለነበረ። በሰዓቱ የሚመጡና የሚሄዱ፤ ሰፊ ሽፋን የሚሰጡ፤ ምቹና በፍጥነት የሚያደርሱ አውቶብሶች የከተማ ባቡሮችና ጀልባዎች በአንድ ወጥ ትኬት አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው የተቀናጁበት የስቶክሆልም የጅምላ መጓጓዣ ስርአት ለማንም ቢሆን የሚያስደንቅ ነው። በሰዓት ስለመምጣትና ስለመሄድ ካነሳን አይቀር የዋስትና ነገር እናንሳ። እንደ ተሳፋሪ አንድ አውቶብስ ወይም ባቡር እየጠበቁ ነው እንበል። ይመጣል ተብሎ ከሚጠበቅበትና አስቀድሞ በወረቀትም በኢንተርኔት ገጸ ድርም ከተለጠፈው ሰዓት አሳልፎ ከሃያ ደቂቃ በላይ ከዘገየ ታክሲ ይዘው መሄድ ይችላሉ። ሂሳቡን የሚከፍለው (የከፈሉትን ሂሳብ የሚመልስልዎ) የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቱን የሚሰጠው ኩባንያ ነው።
ስለሽፋንም ማንሳት ይቻላል። ስቶክሆልም በብዙ ውኃማ አካላት ውብ ቅንብር ከመሆኗ የተነሳ በርካታ ደሴቶች ያሏት ከተማ ነች። አንድ ሁለት በሚሆኑ ደሴቶች መካካል የሚደረግ ጉዞ በሰው መመላለሻ ጀልባዎች የሚከወን ሲሆን በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ተሳፋሪ የጫኑ አውቶብሶችን ከአንድ ደሴት ወደሌላ ደሴት የሚያሻግሩ መኪና ጫኝ መርከቦች አሉ። ከአንድ የከተማው ክፍል ሰው ጭነው የመጡት የከተማዋ አውቶብሶቹ መርከብ ላይ ወጥተው ውኃውን ከተሻገሩ በኋላ ከመርከቡ ወርደው በሄዱበት ደሴት ተሳፋሪያቸውን እንደያዙ ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ። የመልስ ጉዞአቸውንም እንደዛው ሌሎች ተሳፋሪዎችን በሌላ ሰዓት እንደያዙ ወደ መጡበት ክፍል በመርከቦቹ አሻጋሪነት ያስነኩታል።
ስለምቹነት ስናወራ በአውቶብሶቹም ይሁን በባቡሮቹ የሚሳፈር ሰው በጸጥታ የፈለገውን ስራ እየሰራ - የሚነበብም ሆነ የሚጻፍ ነገር ይዞ አልያም ኢንተርኔት ካለው እየተጠቀመ እንዲሄድ - የሚያስችል ነው። የስቶክሆልም ከተማ ባቡሮች እንደ ለንደን፤ ፓሪስና መሰል ከተሞች ባቡሮች ረባሽ ድምጽ የሚፈጥሩ አይደሉም።
በፍጥነት የመድረሳቸው ነገር የሚያያዘው በተለይ ትራፊክ በሚበዛባቸው ዋና ዋና መንገዶች ላይ የህዝብ ማመላለሻዎች የራሳቸው መም ይዘው የሚሄዱ ከመሆናቸው ጋር ነው - ሌሎች መኪኖች የማይጠቀሙበት መም። ኩሬውን  ተሻግሬ (ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ) ወደ ካናዳ  ጠቅልዬ የመጣሁ ጊዜ ግን ከላይ ያሰፈርኳቸው የቀልጣፋና ምቹ የጅምላ መጓጓዣ ስርዓት መገለጫዎች የሉም። አበራታችን ስርአት ሆን ተብሎ በሚመስል መልኩ ካልተፈጠረባቸው  አገሮች በዋናነት አሜሪካና ካናዳ ይገኙበታል።  እርግጥ በካናዳም በአሜሪካም የተሻሉ የሚባሉ ከተሞችም አሉ። በደምሳሳው ግን የሰሜን አሜሪካ ስርዓት ሰው ሁሉ በነፍስ ወከፍ መኪና ይዞ ነዳጅ እየበላ ነዳጅ እየጠጣ እንዲኖር የሚገፋፋ አይነት ነው። የጅምላ መጓጓዥ መረባቸው የመኪና አማራጭ የሌለው ብቻ የሚጠቀምበት፤ ብዙ ቦታ የማይሸፍን ምቹ ያልሆነ የሚባል አይነት ነው።
በአዲስ አበባ የጅምላ መጓጓዣ ተጠቃሚ መሆን ወጪን ይቀንሳል ብቻ ሳይሆን በፍጥነትም ይረዳል። በቅርቡ ያየሁት ከታች ከአዲስ ጎማ አካባቢ (ይመስለኛል) እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ የሚሄደውና  ለህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቻ ተብሎ የተሰራው መንገድ (እውነት ከሆነ - ስላላጣራሁ) በዚህ ረገድ ጥሩ ጅምር ነው። ኪስ አውላቂ ይሰውረንና በአውቶብስ መሄድ - በተለይ መቀመጫ ከተገኘ - ተረጋግቶ ለማንበብም ይሆናል። በቅርቡ የአዲስ አበባ ቆይታዬ በሃይገር አውቶብሶች ተጠቅሜ እንዳየሁት ሩቅ የሚባል የአዲስ አበባ ክፍል ድረስ ለመሄድ የፈጀብኝ ሰዓት ረጅም አልነበረም - በየቦታው ቶሎ ቶሎ ስለማይቆም።   
በጅምላ ማሰብ ብዙ ጊዜ ጥሩ ባይሆንም የጅምላ መጓጓዣ በተመለከተ ግን በጅምላ አስበንበት በጅምላ ብንገባበት የጅምላ ተጠቃሚ እንሆናለን። ብዛታቸውንና ጥራታቸውን በመጨመር በጅምላ መጓዝ ምቹና ማራኪ እንዲሆን ማድረግ ደግሞ አገልግሎቱ የሚሰጡ ድርጅቶች- የመንግሥትም ይሁን የግል - ድርሻ ነው።


 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: