Sunday, November 25, 2012

ደን-በላ ኩባንያዎችን ወዲያ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ግንቦት 11 ቀን  2004 ዓ.ም.) በአዲስ ጉዳይ መጽሔት በዚህ የአረንጓዴ ጉዳይ አምድ የበኩር ጽሑፌን ከጻፈኩ እነሆ አንድ ዓመት ከሦስት ወር አለፈኝ። የጽሑፉ ማጠንጠኛ ዛሬም የተመለስኩበት ርእስ የባዮዲዝል ነገር ሲሆን የተለያዩ ነጥቦች የተነሱበት ነበር። በአገራችን በቀጥታ ለሰው ምግብ ከማይውሉና ለባዮዲዝል ጥሬ እቃነት ይሆናሉ ከተባሉት ጥሬ እቃዎች መካከል በዋናነት ጃትሮፋንና ጉሎን እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ የፓልም ዘይት እንደሚገኙበት አይተን ነበር። በወቅቱ በነበረው መረጃ ወደ ሰባ የሚጠጉ ባለሃብቶች ጃትሮፋን በማልማት ሥራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደዋል መባሉን፤ ከነዚሁ ወደ አሥራ አምስት የሚሆኑት ደግሞ ባለሀብቶች በደቡብ ኢትዮጵያ፤ በአማራ፤ በኦሮሚያ፤ በትግራይ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ እንደተነገረ ወዘተ አንስተን ነበር።

በንድፈ ሃሳብ ደረጃ እንደ ብዙኃን መገናኛዎች ትንተና፤ እንደ ኩባንያዎች ማብራሪያና እንደ መንግሥታት መግለጫዎች ጃትሮፋ በቀላሉና ‘የትም’ የሚበቀል ብዙ ጥቅሞችን የሚሰጥ ተክል ነው  የተባለለት ነበር። እንደ አፋቸው ያድርግልንና ብለንም ተመራርቀን ነበር። እንሰራለን ብለው ይገቡ የነበሩ ኩባንያዎች አካሄድ ሰላም የማይሰጥ ስለነበርና ጃትሮፋን በተመለከተ በተግባር የተደገፈ የአገር ውስጥ ልምድም ሳይኖር ከላይ ጀምሮ ይነገር የነበረው በጎ በጎ ነገሩን ብቻ በመምረጥ ስለበር የ‘አሜን ይሁን ይደረግ ይደረግ’  ምርቃት አስፈላጊ ነበር። በዛን ጊዜ እንዳነሳነው የባዮዲዝል ልማት አዳዲስ ስራዎችን ሲፈጠር ስራው ጥራትና ቋሚነት ወሳኝ ነው።  ለገዛ ሠራተኞቹ ደመወዝ ለወራት አልከፍል ብሎ የነበረው  Flora EcoPower የተባለው የጀርመን ኩባንያ እንደ ምሳሌ አይተነው ነበር - በወቅቱ። ገበሬዎች ኩባንያ ስራ ገቢያቸው እንደሚጨምር ተነግሯቸው መደበኛ ስራቸውን የሚተውበት አጋጣሚና ተስፋው ሳይሆን የቀረበት ሁኔታም ነበር የበለጠ ገቢ ያስገኛል በሚል ሃሳብ መሬታቸውን ለጃትሮፋ ያደረጉ ገበሬዎች የተጠበቀው ምርትና ገቢም አለማስገኘቱ የሚያጠፉት ጊዜ፡ ያልለመዱት ግብአት ለመግዛት ከሚያወጡት ወጪና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ የሚመጣው ችግር ገበሬዎቹን ለአዳዲስና ተጨማሪ ችግሮች ማጋለጡ አልቀረም።  ያልተሳካለት ኩባንያ ሸክም ገበሬው ላይ የመጣል መዘዝ ሊያመጣ የሚችል አሰራር ቀድሞውኑ መኖር አልነበረበትም።
ጉዳይ አስፈጻሚ ወይስ ባለጉዳይ?
ሲጀመር የተደራዳሪነትና የዘላቂ ጥቅም አስጠባቂነት አቅም በሌላቸው የእኛ አይነቱ አገሮች ላይ በውጪ ኩባንያዎች ላይ ተማምኖ የሚሰራ ነገር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ነው። የአፍሪካ አገሮች ከውጪ ኩባንያዎች  ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸው አገራዊ ጥቅምን አስጠብቆ የመስራት ችግር ሰሞኑን በአዲስ አባባ የውይይት አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። ባለፈው ሳምንት በመዲናችን ውስጥ የተካሄደውና አፍሪካ ላይ ያተኮረው የዓለም የምጣኔ ሀብት መድረክ በቀጥታ በኢንተርኔት ለመከታተል ችዬ ነበር። ቀልቤን ከሳቡት የፓነል ውይይቶች መካከል አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከናይጄሪያው ጉድላክ ጆናታን እና ከሌሎች ሁለት መሪዎች ጋር ሆነው ከመድረክ መሪውና ከተመልካቾች ይቀርቡ የነበሩትን ጥያቄዎች የመለሱበት ፓነል ነበር። ከደቡብ አፍሪካ ነኝ ያለች አንዲት ወጣት የአፍሪካ መሪዎች ወጣት ሆነው ምረጡኝ ሲሉ ባለራዕይ ሆነውና በጎ ገጽታ ይዘው ሲሆን ስልጣን ላይ ሲወጡ ግን ተቀይረው ሌላ ነገር የሚሆኑት ለምንድ ነው የሚል አይነት ሃሳብ ያለው ጥያቄ  ጠየቀች። የመጀመሪያው መላሽ አቶ መለስ ነበሩ። ዘለግ ካለው መልሳቸው መካከል የውጪ ኩባንያዎች እንዲገቡ ማድረግ አፍሪካ ውስጥ ከባድ እንደሆነ ኩባንያዎች የሚያገኙት ትርፍ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ማረጋገጫ ካላገኙ እሺ ብለው እንደማይመጡ፤ ከመጡም በኋላ ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ የመንግሥታቱ (የመሪዎቹ) ሚና የሚከፈለው ወይም የማይከፈለው ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ መስራት እንደሆነ የሚገልጽ ይገኝበታል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መነጽርነት በባዮዲዝል ልማት በኩል የሚታየው ችግር ስንመለከተው ምናልባት በባዮዲዝል ጉዳይ ላይ መንግሥት እንደ ባለ ጉዳይ ሳይሆን እንደ ጉዳይ አስፈጻሚ ከመስራቱ ጋር የሚገናኝ ነገር የለውም ማለት ቀላል አይመስለኝም።

ለዚያውም ጉዳዩም ላይፈጸም - ጉዳዩ ባዮዲዝልን አምርቶ የአገሪቱን የውጪ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ ነው የሚለው ላይ ከተስማማን።
የዚህ አሰራር አንዱ ውጤት እንመልከት። የእንግሊዝ ኩባንያ የሆነው ናሽናል ባዮዲዝል (ሰን ባዮፊውል) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 80,000 ሔክታር መሬት ተረክቦ ደኑን ከመነጠረ በኋላ መሬቱ ለታሰበው ምርት አመቺ እንዳልሆነ ገልጾ ሲለቅ ላጠፋው ጥፋት እንኳን ተገቢውን ካሳ ሳይከፍል ቀርቷል። መንግሥት ኩባንያው መጀመርያ  ጥናት አጥንቶ ያዋጣኛል ብሎ ሲገባ የጥናቱን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ካልሆነም እንደዛ ሲያደርግ ዋጋውን መክፈል አለበት። ይህን ያህል ሰፊ መሬት ደኑ ተጨፍጭፎ “የእርስዎም ይሞክሩት” ሜዳ መሆን አልነበረበትም።

የመንግሥት መልስ በሁለቱም በኩል  ልምዱ አልነበረንም፤  ክትትል የማድረግና ይህንን ለማስፈጸም ውል ራሱ አልነበረንም የሚል ነው። ትንንሽ ትምህርቶች ለመማር ትልልቅ ስህተቶች የግድ መሰራት የለባቸውም።
ይልቁንም የተፈጠሩት ችግሮች መንግሥት አስቀድሞ የያዘው አቅጣጫ አስተካክሎና በአገር ውስጥ ባሉ ሀብቶችና ግብአቶች ማድረግ የሚችለው ነገር ቢያደርግ ኖሮ ማስቀረት የሚችላቸው ችግሮች ነበሩ።
እስካሁን ያልነው በመጀመሪያም ጽሑፍ የተባለ ነው - ከሞላ ጎደል። ዛሬም ለማንሳት ያስፈለገው  ግን እነሆ ከዓመት በላይ ካለፈ በኋላም መሬት ተረክበው  ምንጣሮ አካሂደው ‘ስራ’ ጀምረው ከነበሩት ኩባንያዎች መካከል አብዛኛዎቹ (ስድስት ሲቀሩ) ስራቸውን ማቋረጣቸውንና ራቸውን ማግለላቸውን በቅርቡ መዘገቡ ነው። ስራውን ከተዉት መካከል የአገር ውስጡ አምባሰል ትሪዲንግ እንደሚገኝበት ተነግሯል። የዛሬ ስድስት ዓመት በናሽናል ባዮዲዝል (ሰን ባዮፊውል) ፋና ወጊነት (መሬት ወይም ደን ወጊነት እንበለው ይሆን?) የተከፈተው የባዮዲዝል መድረክ አሁንም ድረስ ደን በመመንጠር፤ ከተፈቀደላቸው ስራ ውጪ የሆነውን ከሰል የማክሰልና የመሳሰሉት ነገሮች ውስጥ የሚገቡና ከዛ በቃን ብለው በሚወጡ  ደን-በላ ኩባንያዎች ዛሬ ድረስ ነጻ መሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ባለኝ መረጃ መሰረት (ለመረጃው ጥራት አልምልም እንጂ) እስካሁን ደህና ስራ ሰራ የሚባለው የአማራ መልሶ መቋቋም ልማት ድርጅት ነው።  ቢያንስ የጃትሮፋ መጭመቂያ ተከላ ፈጽሟል። አሁንም በዘይት ጨመቃ የተወሰነ ነው እንጂ በአማራ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ከተለያዩ ቦታ የተገኑ የጃትሮፋ ዝርያዎችን የዘይት መጠን በፐርሰንትና በሄክታር የሚገኘው የምርት መጠን በቶን አጥንቶ በየት የት ቦታ ላይ ማልማት እንደሚቻል ያደረጉት ጥናት ይበል የሚያሰኝ ነው።
መንግሥት በፌደራል ደረጃ ከዚህ በላይ መሄድ አለበት። በሁለት ነገሮች ላይ የማብቃት ስራ መስራት አለበት - የምጣኔ ሀብታዊና የቴክኖሎጂ ብቃት።

የምጣኔ ሀብታዊ ብቃት
አገሪቱ ከተለያዩ ምንጮች ከምታገኘው ገቢ ውስጥ የተወሰነውን ወሳኝ እና በሌላ አካል ሊሰሩ የማይችሉ ወይም ሌሎች አካላት ሊሰሩዋቸው ፈቃደኛ የማይሆኑባቸው ዘርፎች በመንግሥት እንዲሰሩ ለማድረግ መዋል አለበት። ለዚህ ስራ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ መንገዶችን የመፈለግ ስራ መስራት ይጠበቅበታል። ከውስጥም የውጪም የሚገኘው ገንዘብ በአግባቡና በግልጽ አሰራር ያለ ብክነት በተገቢው ቦታና ጊዜ ላይ ጥቅም ላይ ሲውል በቀጣይ ገንዘብ ለማግኘት ቀና መንገድ ስለሚፈጥር በጥንቃቄ የተሰራና በደንብ የታሰበበት አካሄድ የግድ ይላል።
የቴክኖሎጂ ብቃት
ባዮዲዝልን ከጥሬው የዘይት ፍሬ ለማምረት ያን ያህል ውስብስብ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ነገር አይደለም። በአገሪቱ ያሉ ለተለያየ ዓላማ የተቋቋሙ የመንግሥትም የግልም ኩባንያዎች ያላቸው የማምረቻ ብቃት በማስተባበር ሊሰሩ የሚችሉ የባዮዲዝል ማምረቻ እቃዎች ብቻ ናቸው የሚያስፈልጉት።
አንዱ ኩባንያ ወይም ድርጅት መጭመቂያውን ሊሰራ ይችላል። ሌላው ደግሞ ዘይቱን ከዝቃጩ የሚለየውን ይሰራል። የኬሚካል ማብሊያውን ደግሞ ሌላው ይሰራዋል። እንደዛ እንደዛ እያለ ይቀጥላል። ከሚያስፈልጉት ግብአቶች አንዱ  ኤታኖል ወይም ሜታኖል ከተባሉት የአልኮሆል አይነቶች አንዱ ሲሆን እንደተመረጠው የምርት ሂደት ደግሞ ለምሳሌ የአሲድ አቃጣሪ ያስፈልጋል።  ከዘይቱ ሌላ ያሉት እነዚህ የኬሚካል ግብአቶች ደግሞ በሌሎች የአገር ውስጥ አምራቾች እየተመረቱ ያሉ ወይም በቀላሉ መመረት የሚችሉ ናቸው (ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት)።
አንድ የቴክኖሎጂ ብቃት መገንባት ማለት በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሌላ የቴክኖሎጂ ብቃት ለማምጣት የሚያስፈል ስራን መለኮስ ማለት ነው። ያ ደግሞ በተራው ሌላ ስራን እየለኮሰ የቴክኖሎጂ ብቃት ስራ እየተቀጣጠለ ሲሄድ አገሪቱ የሚያስፈልጋት የኢንዱስትሪ ምጥቀት እውን ለማድረግ የራሱ ድርሻ ለመወጣት እድሉ ሰፊ ይሆናል። የዚህ ተቀጣጣይ ልማት ጥቅሙ ደግሞ ዘርፈ-ብዙ ነው። ለብዙ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል። ለብዙ ስራዎች ገበያ ይፈጥራል። ለብዙ ገበያዎች በቂ አቅርቦት ይሰጣል።
በአገሪቱ አነሰም በዛም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ በብረታ ብረትና ተያያዥ የምህንድስና ስራዎችን የሚሰሩ ኩባንያዎች አሉ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የመሰረታዊ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ማኅበር አባላት የሆኑ አምሳ አራት የሚሆኑ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ የየራሳቸው አቅምና ትኩረት ያላቸው ናቸው። በዛ ላይ ደግሞ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፤ ከብረታ ብረትና ከተመሳሳይ ሥራዎች ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለዚህ ሁሉ ስራ ሰፊ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ።
በመደበኛ የነጻ ገበያ እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የሚፎካከሩና ለየብቻቸው ለመስራት የተቋቋሙ ቢሆንም በእንደዚህ አይነት በብሔራዊ አጀንዳነት ደረጃ መታየት የሚገባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንደየድርሻቸው የየራሳቸው ጥቅም እያገኙ ግን በመቀናጀት የአገራችንን የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት በምናደርገው ጥረት አገራዊ ሚናቸውን መጫወት እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደዚህ አይነት ስራዎች በጋራ በሚሰሩበት ጊዜ ከታች ያሉት ኩባንያዎች ደረጃቸውን ከፍ የሚያደርጉበት ፤ከፍ ያለ ደረጃ ያሉት ደግሞ ዋና ዋና ስራዎችን በሚሰሩበት ጊዜ ሌሎች የግብአት ስራዎችን ከነሱ አነስ ላሉት ድርጅቶች እንዲሰጡ እድል ይፈጥርላቸዋል - ተጠቅሞ በመጥቀም አሰራር። ይህን ታላቅ ስራ ለመስራትና ስራዎቹን በገንቢ መስመር ለማስተባበር ጥሩ የቅንጅት ስራን ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ከመንግሥትም ከግል ዘርፉ በሚመጡ ክፍሎች የሚቋቋም አስተባባሪ አካል ያስፈልገዋል።

ጥናት ሳያደርጉ የሚመጡ ኩባንያዎች የሚፈጥሩት ችግር ለማስቀረት በአገሪቱ ያሉት የመንግሥትም ይሁኑ የግል ዩኒቨስርቲዎችና ኮሌጆች በዘርፉ ዙሪያ ከመለስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ጥናቶች እንዲያደርጉ አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል። ለዛም የሚሆን ድጋፍ በመስጠት ጥናቶቹን ‘ኮሚሽን’ ማድረግ ተገቢ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያጠኑትን ጥናት ስራ ላይ ማዋል ለትምህርት ተቋማቱም ለመንግሥትም በአጠቃላይ ለአገሪቱ በጣም ጠቃሚ ይሆናል።
አሳዝኙ ነገር አሁንም መንግሥት በቅርቡ በአንድ መድረክ እንደተናገረው ‘ይሄ የግሉ ዘርፍ እንጂ የእኔን እጅ የሚፈልግ አይደለም’ እያለ ለደን-በላ ኩባንያዎች ‘ተጨማሪ ማበረታቻ’ መስጠት ነው የሚያዋጣው ብሎ ማመኑ ነው።

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: