Sunday, November 25, 2012

‘ብርቱው የአፍሪካ ተደራዳሪ - አፍሪካ በበርካታ ግንባሮች ታጣዋለች።’


(ጌታቸው አሰፋ፤ መስከረም 4  ቀን  2004 ዓ.ም.) በዚህ ሳምንት በሞት የተለዩንን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊን ከአዛላቂ ልማት አኳያ የነበራቸውን ሚና በጥቂቱ በማንሳት አስባቸዋለሁ።እንደአለመታደል  ሆኖ እሳቸውም ሳይጽፉ ስላረፉ ወይም በሌሎች ስለሳቸው የተጻፉት ነገሮችም ቢሆኑ በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን የዕለት ተዕለት ውሎዋቸውን በሚያሳይ መልኩ በዝርዝር አይደለም። እናም ይህን ስጽፍ የምጠቀምባቸው ምንጮች በስራ ዓለም ካወቅኋቸው አጋጣሚዎች በመነሳት ነው።
ለአዘላቂ  ልማት መሳካት ወሳኙ ነገር የኃይል ምንጭ እንደሆነ የታወቀ ነው በዚህ ዓምድም በተደጋጋሚ እንደተባለው። ስለ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ከወራት በፊት ስጽፍ ያነሳሁት አንድ ገጠመኝ እዚህም ላይ አስፈላጊ ነውና ይደገማል። 
ወደ ጀልባው የገባሁት ዘግይቼ ነበር። ያልተያዘ ወንበር ያለበት ጠረጴዛ ስፈልግ አንድ ብቻውን የተቀመጠ ሰው አየሁና ሄጄ ተቀላቀልኩ። ተዋወቅኩት። ይህ የሆነው የዛሬ ሰባት ዓመት ካናዳ ቶሮንቶ ነው። ከየአገሩ የተሰባሰብን የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ማብቂያ ላይ በኦንታሪዮ ሐይቅ እየተዟዟርን ለምንበላው እራት ነው ጀልባው ውስጥ የተገኘነው። ‘ከየት ነህ?’ አልኩት። ‘ከዚሁ ከካናዳ ነኝ። ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ነው የማስተምረው’ አለኝ። እኔም ተጠየቅኩ። ‘ከኢትዮጵያ ነኝ። አሁን ግን ስዊድን ነው ያለሁት’ ብዬ የነበርኩበትን ዩኒቨርሲቲ ነገርኩት። መልኩ ‘መሠረትህ ግን ከየት ነው?’ እንድለው ገፋፋኝ። ገና “ከግብጽ” ከማለቱ ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ። ‘በጣም ጥሩ አጋጣሚ….. በመንግሥት ደረጃ ሳይሆን በተራ ግብጻዊ ደረጃ ስለአባይ የሚሰማችሁ ነገር እስቲ ንገረኝ።’ የፊቱ  ቀለም ተቀያየረ። ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ሆን ብለው ለግብጽ ጥፋት የሚሰሩ መሆኑን ከአባይ ጋር በተያያዘም ጉልበታቸውን ለግብጽ ለማሳየት በኤርትራና በሱማሊያ ጦርነት እንደጫሩም ነገረኝ - በስሜት።
መለስ ዜናዊ ጡንቻቸውን በአፍሪካ ቀንድ የሚያሳዩት ቀስ በቀስ የአባይን ግድብ ገድበው ግብጾችን ችግር ውስጥ ለመክተት እንደሆነ አጫወተኝ። ለኔ ይህ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በአባይ ጉዳይ ዙሪያ ውስጥ ለውስጥ የምር የያዙት ነገር እንደነበር አመላካች ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን የማላገኘውን መረጃ ለማነፍነፍ መጣር ጀመርኩ።
ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በጣም አንባቢና በብዙ ነገሮች ዙሪያ መረጃ ጠገብ ነበሩ። በቅርብ የሚያውቋቸውና አብሯቸው የሰሩ የአገር ቤትም የውጪም ሰዎች የሚመሰክሩላቸውም ይህንኑ ነው።
ጀፈሪ ሳክስ ጋናዊው  ኮፊ አናን የተመድ ዋና ጸሀፊ በነበሩበት ወቅት አማካሪያቸው ነበሩ። ዋና ስራቸው በምእተ ዓመቱ ግቦች ጉዳዮች ዙሪያ ነው። በዛው ጉዳይ የአሁኑን የተመድ ዋና ጸሀፊ የሆኑት ኮሪያዊውን ባንኪ ሙንንም ያማክራሉ። እኚህ ምሁርና ብዙ መንግሥታትን ያማከሩ ሰው ኒወርክ በሚገኘው የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የኧርዝ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና ፕሮፌሰር ሲሆኑ The End of Poverty:  Economic Possibilities for Our Time  እና  Common Wealth- Economics for a Crowded Planet የሚሉ መጽሐፍቶችን ያበረከቱ ናቸው። የመጀመሪያውን መጽሐፍ ለማስተማር እጠቀምበት የነበረና አቶ መለስን በምሳሌነት የሚነሱበት ነው። እኝህ አሜሪካዊ ምሁር የጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ዋና አድናቂ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን የየአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ላይ ወሳኝ ነገሮችን የተማሩት ከቀድሞው የእንግሊዝ ሌበር-መራሽ መንግሥት አማካሪ ከነበሩትና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን ከገንዘብ ስሌት ጋር በማቀናጀት ከሚታወቁት ጌታ ኒኮላስ ስተርን ነው። የዛሬ ሦስት ዓመት ለኮፐንሀገን ዝግጅት ሲባል አዲስ አበባ ተደርጎ በነበረ አንድ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ‘በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተማሩኝ ጥሩ ወዳጄ’  በማለት አሞካሽተዋቸው ነበር። እኚህም ሰው የመለስ አድናቂና የቅርብ ሰው ነበሩ።
ሌሎች ሰዎች ደግሞ አቶ መለስን የሚያደንቁት በአንድ አጋጣሚና ጉዳይ ዙሪያ ባገኝዋቸው ጊዜ በሚፈጠረው ሁኔታ ነበር። የኢትዮጵያ የቅርብና የረጅም ዘመን ወዳጅ የሆኑትና ራሳቸውን ፊታውራሪ ሊበን ገብረ ኢትዮጵያ እያሉ የሚጠሩት አሜሪካዊው የቺካጎ ዩኒቨርስቲ የሶሽዮሎጂ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሌቭን ልጅ ቢል ሌቭን በፊልም ስራ ለረጅም ጊዜ ከሰራ በኋላ ወደታዳሽ ኃይልና ምርቶች የስራ መስክ ውስጥ ሲገባ መስራት የፈለገው የአባቱ የፍቅር አገር በሆነችው በኢትዮጵያ ላይ ነበር። በ1991 ዓ.ም. በጀመርኩት በኢትዮጵያ የአካባቢና የኃይል ጉዳዮች ዙሪያ በምጽፍበት ‘akababi.org’ በተባለው ገጸ ድር ምክንያት ከአባቱም ከልጁም ጋር ተዋወቅን - በኢ-ሜይል። በአካል የተገናኘነው ግን በ2006 እ.አ.አ. እኔም ከስዊድን ወደ አዲስ አበባ የአፍሪካ ባዮኢነርጂ ኮንፈረንስ ኢስኤ ላይ ሲደረግ ለመሳተፍ መጥቼ እነሱም ለመሳተፍና ለሌላ ጉዳይ መጥተው ነበር። ያ ሌላ ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊን ማግኘት እንደሆነ የነገሩኝ እንደከሰዓት ሊገቡ ጠዋት የሆነ ቀጠሮ ለመያዝ አመቺ ሰዓት ስንመርጥ ነበር። አቶ መለስ ጋ የሚያስኬዳቸው ጉዳይ ‘ኦርጋኒክ አስፋልት’ የሚባል ሀሳብ ይዘው በመምጣታቸው መንግሥት ከሚያራምደው የመንገድ ማስፋፋት ስራ አንጻር እንዴት እንደሚያያው ከዋናው ለመስማትና ወደ ስራ ለመግባት ነበር። በማግስቱ ስንገናኝ የኔ ጥያቄ “ምን አሉ?” የሚል ነበር። ቢልን የመሰጠው መልስ “ጥሬ ዕቃው ሙሉ በሙሉ እዚህ አገር ውስጥ የሚመረትበት መንገድ ፈልጉ?” የሚል ነበር።  አዎ ከአካባቢያዊ አዛላቂነት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከምጣኔ ሀብታዊ አዋጪነት አኳያ በአገር ውስጥ ከሚገኝ ጥሬ እቃ የሚመረት ምርት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለውና የአቶ መለስ ጥያቄ ተገቢነት ላይ ተስማምተን አደነቅን።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከኮፐንሀገን ጀምሮ ሜክሲኮ ካንኩን በተደረገውም ከዛም መጨረሻ ላይ አምና ደርባን ደቡብ አፍሪካ በተደረገውም የአየር ንብረት ለውጥ ድርድርም የአፍሪካ ቡድን ዋና መሪ ተደራዳሪ ሆነው በአፍሪካ  መሪዎች በመመረጥ አገልግለዋል። በዴንማርክ ኮፐንሀገን በተደረገው የሉላዊ አረንጓዴ እድገት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ በ2030 እ.አ.አ. የልቀት መጠን ጭማሪዋን ዜሮ ለማድረግ እንደምትሰራ ተናግረው ከዛም አምና በደርባን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራተጂያቸውን ይፋ ሲያደርጉ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝተዋል።
ከኮፐንሀገኑ ስምምነት ሦስት ወር በኋላ በነበረው የካቲት ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሰያሚነት የገንዘብ ድጋፉን ከየት ሊገኝ እንደሚችል አጥንቶ እንዲያቀርብ የተቋቋመውን ቡድን ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊና ከኖርዌዩ አቻቸው የንስ ስቶልተንቤሪ ጋር በመሆን በሰብሳቢነት የሚመሩት ነበር።
በእነ አቶ መለስ በኩል እንደመነሻ  የቀረበው ሪፓርት ላይ አርባ አገሮች በሚሳተፉበት ቡድን ለአንድ ዓመት በተደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ሲዳብር ቆይቶ ነበር። 
በአቶ መለስ መሪነት ታዳጊ አገሮች ፈንዱ እስካሁን በሌላ ስም ለተረጂ አገሮች ሲሰጥ የቆየውን ገንዘብ አሁን አዲስ የስም መጠቅለያ ብቻ በመቀየር የሚሰጥ እንዳይሆን ስጋታቸውን በአጽንኦት ገልጸው ነበር። ይህን ስጋት ከሚያስወግዱት መካከል ገንዘቡ በከፊል ከዓለም አቀፍ የባህር ትራንዚት፤ከአየር ጉዞ ቲኬትና ፤ ከገንዝብ ልውውጥ አገልግሎት በፐርሰንት መሰበስብ ከሚያስችል አዲስ ምንጭ ይገኛል መባሉ ነው። የዚህን ፈንድ እውን መሆንና ተግባራዊነት በተመለከተ ጠቃሚ ውሳኔ እንዲተላለፍ ከመልፋት አንጻር የአቶ መለስ ዜናዊ አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር።
የአቶ መለስ ዜናዊ እረፍት እንደተሰማ በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ዙሪያ የአፍሪካ መሪ ጠንካራ ድምጽ እንደነበሩ ከተለያዩ የአፍሪካና የዓለም መሪዎች የተገለጸውና በተለያዩ ሚዲያዎች የወጣው የአድናቆት መልእክት ለአገር ቤት አንባቢና ተመልካች የደረሰ ስለሆነ እዚህ ላይ አላነሳውም። በአካባቢ ምህንድስናና በአዛላቂ መሰረተ ልማት መስክ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሆኜ በስዊድን በምማርበት ጊዜ አብራኝ የተማረችው ታንዛናዊቷ ኪሳ ምፋሊላ አሁን የምትሰራው ለአፍሪካ ልማት ባንክ ነው። የጠቅላይ ሚኒስተራችን እረፍት እንደሰማች በፌስ ቡክ ያሰፈረችው የመሪዎችን ድምጽ የሚያስተጋባ ነው፡ “መለስ ዜናዊ - በአየር ንብረት ለውጥ ንግግሮች ሁሉ ብርቱው የአፍሪካ ተደራዳሪ። አፍሪካ በበርካታ ግንባሮች ታጣዋለች” የሚል ነበር። ነፍስ ይማር! መጽናናትን ለዘመድ ለወዳጅ!

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: