Sunday, November 25, 2012

ባለሦስት ስለቱ ኸሪከን


(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥቅምት 30  ቀን  2004 ዓ.ም.)በአሜሪካና በካናዳ ምስራቃዊ ዳርቻ ከተሞች የዚህ ሳምንት ሰኞና ማክሰኞ እንደወትሮው አልሆኑም። በብዙኃን መገናኛዎች እንደተከታተላችሁት ሳንዲ ተብሎ በሚጠራው ጋላቢ ማዕበል(ኸሪከን) ሚልዮኖች ለችግር ተጋልጠዋል። በውሃ ነፋስ እና እሳት ስለት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአትላንቲክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚከሰተውና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ማዕበል ‘ኸሪከን’ ተብሎ ይታወቃል።
ብዙውን ጊዜ ከምድር ወገብ ከፍ ብሎ ከምስራቅ በኩል ወደ ምዕራብ የሚመጣ ነው። የክስተቱ መነሻ ከገጸ ውቅያኖስ ሙቀት መጨመር ጋር ይያዛል። ከውቅያኖሱ በላይ ያለ ሞቃትና እጥርበት-አዘል አየር ሲቀዝቅዝ ዝናብ ይፈጥራል። በሂደቱም ተሸክሞት የነበረውን ከፍተኛ ኃይል ያራግፋል። ይህም ኃይለኛ ነፋስ ይፈጥራል። እንደገና የውኃ ትነትን ያስከትላል። ይህም በተራው ይቀዘቅዛል። ሌላ ዙር ዝናብና ነፋስ ይፈጠራል። እንዲህ እያለ በድግግሞሽ ሽክርክሪት ይቀጥላል። በመቶዎች ኪሎሜትሮች መጠን ያለው ጋዝ-ጠገብ የሻምፓኝ ጠርሙስ ተነቅንቆ ሲከፈት ሊፈጥር የሚችለውን ነገር ያስቡት።  የኸሪከን ቅርጽ እየተሸከረክረ የሚሄድ ባለ አይን ክብ ሲሆን መሐል ላይ ያለው ‘አይን’ የምንለው ክፍል በንጽጽር ጸጥ ያለ ነው። በአይኑ ዙሪያ የሚሽከረከረው ክፍል ግን በዝናብና በነፋስ የተሞላ የተቀወጠ ክፍል ነው። የሙሉ አካሉ ከጫፍ እስከ እስከ ጫፍ ርዝመት ከ480- 1125 ኪ.ሜ ድረስ ይደርሳል። የአይኑ ብቻ 16-48 ኪ.ሜ ይሆናል። እርግጥ ጠቅላላ  ርዝመት በተመለከተ በሰሜን ምእራብ ሰላማዊ ውቅያኖስ የሚከሰተውንና ታይፉን ተብሎ የሚጠራውን ተመሳሳይ ክስተት አንድ ላይ አድርገን ካየነው በጣም ትንሹ የሚባለው ከ 444 ኪ.ሜ በታች የሆነው ነው። መካከለኛ ርዝመት በ666 እና 1340 ኪ.ሜ ሲሆን በጣም ትልቅ የምለው ደግሞ 1776 ኪ.ሜ ያለው ነው። በሰሜን አትላንቲክ አካባቢ የሚከሰቱት እንደ ሳንዲ የመሳሰሉት ኸሪከኖች ከታይፉኖች በግማሽ ያክል የስፋት መጠን ሊቀንሱ ይችላሉ። በንጽጽር ጸጥ ያለ ነው የሚባለው የአይኑ ክፍል የነፋሱ ፍጥነት ከ16 እስከ 25 ኪ.ሜ በሰዓት የሚደርስ ሲሆን  ወደ ላይ ከፍታው እስከ 15 ኪ.ሜ ይሆናል።  የውቅያኖስ ላይ ማዕበሎች እንደ ፍጥነታቸው በሦስት ይከፈላሉ።  እስከ 63 ኪ.ሜ  በሰዓት የሚኖግደው ትሮፒካል ስጥመት የሚባለው ሲሆን እስከ  119 ኪ.ሜ የሚጋልበው ትሮፒካል ማዕበል ተብሎ ይታወቃል። ከ119 ኪ.ሜ በላይ ከሆነ ነው ኸሪከን ወይም ታይፉን የሚባለው። እነዚህ ጋላቢ ማዕበሎች ወይም ኸሪከኖች ደግሞ አሁንም እንደ ፍጥነታቸው በአምስት ደረጃ ይከፈላሉ።  እነሱም፤
  • ደረጃ አንድ   ከ119 እስከ 133  .. በሰዓት            
  • ደረጃ ሁለት  135 እስከ 165 .. በሰዓት
  • ደረጃ ሦስት ከ170  እስከ 211  .. በሰዓት
  • ደረጃ አራት  213 እስከ 250 .. በሰዓት
  • ደረጃ አምስት  252 .. በሰዓት በላይ ናቸው።
አሁን ያለንበት ወቅቱ የኸሪከን ወቅት ነው። ልክ እኛ ዝናብ ሰኔ፤ ሐምሌና ነሐሴ ላይ እንደምንጠብቀው ሁሉ እነ አሜሪካና ካናዳም ከጁን አንድ እስከ ኖቬምበር ሰላሳ ድረስ ባለው ወቅት ኸሪከኖችን ይጠብቃሉ።  በቁጥር ሳይቀር በአንድ ወቅት (በየዓመቱ) ስም የሚሰጣቸው እስከ አስራ አንድ የሚደርሱ ኸሪከኖች ይጠበቃሉ - በደህናው ዓመት (በደህናው ቀን እንዲሉ)።የኸሪከን ሳንዲ ስፋት ሽፋን ከ1600 ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን የሚጋልብበት ፍጥነት 45 ኪሎ ሜትር በሰዓት ነበር። የነፋሱ ፍጥነት ደግሞ 145 ኪሎ ሜትር በሰዓት ነበር። ሳንዲ አሜሪካንና ካናዳን ከመምታቱ ከሃያ ሰባት ቀናት በፊት ነበር በካሪቢያን አገሮች አካባቢ የጀመረው። ከታች ወደ ላይ በሚመጣበት ጊዜም እነ ሄይቲ፤ ኩባ፤ ባሃማስ፤ ዶሞኒካን ሪፐብሊክ፤ ጃማይካንና ፖርቶ ሪኮን ረጋግጦ ነው የመጣው።
ያደረሰው ጥፋት
ኸሪከኖች እንደዛ እያሽከረከረ የሚያጋልባቸው ኃይል መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚያደርሱት ውድመትም ቀላል አይደለም። አንድ አማካይ ኸሪከን የሚለቀው የኃይል መጠን በዓለማችን ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ሁለት መቶ እጥፍ ይሆናል። ሳንዲ የሸፈነው ስፋት ስምንት አገሮች ሲሆን በአሜሪካ ብቻ በርካታ ስቴቶችን ነካክቷል። ከሰው ሕይወት አኳያ ይህን ጽሁፍ እስከጻፍኩበት ድረስ በስምንት አገሮች ውስጥ ለመቶ ሃያ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል።
በአሜሪካ ወደ አስራ ስምንት ስቴቶች ውስጥ የመብራት መቋረጥ፤ ወደ አስር ስስቴቶች የስልክ መቋረጥ እንዲሁም ወደ አስራ ሁለት ስቴቶች ሰዎች ቦታቸውን እንዲለቁ ሲያደርግ፤ ወደ አስራ ስድስት ስቴቶች ውስጥ ደግሞ ሰዎች በቀይ መስቀል መጠሊያዎች ለመጠለል እንዲገደዱ ምክንያት ሆኗል። ወደ ስምንት ስቴቶች ውስጥ ደግሞ ሰዎች ሞተዋል።ውኃና ነፋስ ብቻ አይደለም የማዕበሉ የጥፋት መገለጫ። እሳት የሳንዲ ሦስተኛው የጥፋት ስለቱ ነበር። በእሳትም ጭምር ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ነፋሱ መስመሮችን ሲበጣጥስ በየኤሌከትሪክ ትራንስፎርመሩ ውስጥም ውሃ እየገባ ፍንዳታዎች ሲከሰቱ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ለማጥፋት በማይችሉበት ሁኔታ እሳቶች በየቦታው እየተነሱ ነበር። በኒውዮርክ ብቻ ወደ ሃያ ሦስት ቦታዎች ልይ እሳት ተነስቶ ነበር።  ያለምንም ከልካይ ሰማንያ ቤቶችን ያወደመው  እሳት አንዱ ነው። ወደ ስምንት ነጥብ አንድ ሚልዮን ሰዎች በአሜሪካ ከመብራት ሃይል አገልግሎት ውጪ ሆነዋል። የተወሰነው የኒውዮርክ ክፍል ከሳምንት በላይ ያለ መብራት ሊቆይ እንደሚችል እየተገመተ ነው። በካናዳ ኦንታርዮም ወደ 145 000 የሚሆኑ ሰዎች ከመብራት ውጪ ሆነዋል። ከአስራ አምስት ሺህ በላይ በረራዎች ተሰርዘዋል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና መስሪያ ቤት የሆነው ሕንጻም በሁለት ቢልዮን ዶላር ወጪ ሲደረግለት የነበረው እድሳት ላይ ጉዳት ደርሶበታል።በአጠቃላይ በገንዘብ ስሌት እስከ ሃያ ቢልዮን ዶላር የሚደርስ ውድመት እና በተጎዳ ቢዝነስ ደግሞ እስከ ሰላሳ ቢልዮን በድምሩ እስከ ሃምሳ ቢልዮን ዶላር ኪሳራ አድርሷል ተብሎ ይገመታል - ሳንዲ። ይህ ማለት በጣም ከፍተኛ ነው የተባለውን የዘንድሮውን የአገራችን ጠቅላላ ዓመታዊ በጀት ከአምስት እጥፍ በላይ  የሚሆን ነው። በአጭሩ ከአምስት ዓመት በላይ ሊሆን የሚችል በጀታችን  ነው እንክት ያደረገው - ኸሪከን ሳንዲ። በሌላ አባባል ቢያንስ አስር የታላቁ የህዳሴ ግድብን ማሰራት የሚችል ገንዘብ ማለት ነው። በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረገው የአሜሪካ ምርጫ ሳይቀር እንዳይተላለፍ ተሰግቶም ነበር። ነገ እሁድ የሚደረገውና እንቁዎቹ ገብረማርያም ገብረእግዚአብሔርና ቲኪ ገላና የሚሳተፉበት አርባ ሦስተኛው የኒው ዮርክ ማራቶን እንደታቀደው ይደረጋል ተብሏል - ጉዞአቸውን የሰረዙ አትሌቶችን ቢኖሩም።
የአየር ንብረት ለውጥ?
ከአየር ንብረት ለውጥ መገለጫዎች መካከል የባህር ጠለል ከፍ ማለት አንዱ ነው። የኒውዮርክ አካባቢ ያለው ባህር ጠለል በሰላሳ ሳንቲሜትር ከፍ ብሏል - ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር። ሌላው የውኃው ሙቀት መጨመር ነው። የኸሪከን ሳንዲ መጋለቢያ የሆነውና ኒውዮርክን በምስራቅ የሚያዋስናት  የአትላንቲክ ውቅያኖስ ውኃ ከዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ከነበረው ሙቀት በዜሮ ነጥብ ስምንት ጨምሯል። ሞቅ ያለ ውሃ ውስጥ የታዘለው ኃይል ደግሞ ለነውጥኛ ጋላቢ ማዕበሎች ዋና መሸምጠጫ ጉልበታቸው ነው። ከላይ እንዳየነው የኸሪከኖች  ቁጥር በተለመደው እስከ አስራ አንድ የሚደርስ ነበር። ካቻምና 19 አምና ደግሞ 18 ነበር ብዛታቸው። አሁን ወቅቱ ለማለቅ ወደ አንድ ወር ቀርቶትም ቁጥራቸው 19 ደርሷል። የወቅቱ ራሱ ከወትሮው ቀደም ብሎ መጀመርና ዘግይቶ መውጣት፤ የማዕበሎቹ ቁጥር መጨመር እንዲሁም ጎልበታቸውና የጥፋት መጠናቸው ከፍተኛ እየሆነ መምጣት እየታየ ነው። በሳይንሱ ዓለም ‘ምን ሲሆን ምን ይሆናል?’ የሚለው ላይ የተሻለ እርግጠኛነት አለ። አንድ ክስተት ነጥሎ ወስዶ ግን ይህ በእርግጠኝነት በዚህ ምክንያት ነው ለማለት የሚቻልበት ደረጃ ገና ነው። ለምሳሌ የኸሪከን ሳንዲ ክስተት ላይ የአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታወቃል። ኸሪከኑ ግን የአየር ንብረት ለውጥ ባይኖር የማይከሰት በለውጡና በለውጡ ምክንያት ብቻ ነው የተከሰተው አንለውም። የተፈጥሮ ኡደት አካልም ሊሆን ይችላል። የመጨረሻው ዘመን መቃረቢያ የእግዚአብሔር ቁጣም ሊሆን ይችላል። ማን ያውቃል?


 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: