Sunday, November 25, 2012

‘በረከተ መርገም’

(ጌታቸው አሰፋ፤ ነሐሴ 12  ቀን  2004 ዓ.ም.) ርዕሱን የተዋስኩት ተወዳጁ የስቶክሆልሙ ኃይሉ ገብረዮሐንስ ወይም ኃይሉ ገሞራው ከዛሬ አርባ አምስት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት ከጻፈውና  ‘በረከተ መርገም’  የሚል ርዕስ ከነበረው ግጥሙ ነው። ኃይሉ ገሞራው ደራሲ፤ገጣሚና ባለቅኔ ነው።  በ‘በረከተ መርገም’ ያኔ ድሮ ያኔ በዓለማችን በተለያየ ዘመን በተለያየ ቦታ ስለ ተፈለሰፉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንድ በአንድ ፈልሳፊዎቹንም እያነሳ ከተፈጠሩበት ዓላማ ጀርባ ስላላቸው ወይም ሊኖራቸው ስለሚገባው ኅብረተሰባዊ ጠቀሜታ እየጠቆመ ቴክኖሎጂ  በአግባቡ ስንጠቀምበት በረከት ነው በድሃውና በሀብታሙ፤ በተማረውና ባልተማረው፤ በከተሜውና በገጠሬው፤ ‘ባለው’ እና ‘በሌለው’ መካከል ሰፊ ልዩነት የሚፈጠርና ልዩነቱንም በጣም እያሰፋ የሚሄድ ከሆነ  ደግሞ መርገም ነው ይላል። በኃይሉ ገሞራው ‘በረከተ መርገም’ የትችት ስለት የሚተለተሉት በኅብረተሰባዊ ክፍሎች መካከል ያለን ልዩነት በማስፋት አንዱ ወገን ለሌላው ወገን ባርያና አገልጋይ እንዲሆን የሚያደርገው ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂውን የፈጠረውም ሰው ጭምር ነው። 

የሰው ልጅ ዓለምን የሚያድን፤ዓለምንም የሚያጠፋ ቴክኖሎጂ ሰርቷል።  እሳትና የእጅ መሳሪያዎችን መጠቀምን አሻሽሎ በእንፋሎት ገፊነት የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ መፍጠር ሄዷል። ይህ እምርታ ደግሞ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ማሺነሪዎችን ወደ መጠቀም አሸጋግሮታል። ከዚህ እድገት የተነሳም ትልልቅ የኢንዱስትሪ ማምረቻ ፋብሪካዎች መፈጠር ችለዋል በተለይ በአውሮፓ። በአውሮፓዊያን ፋና ወጊነት በተበታተነ ሁኔታና በአነስተኛ ደረጃ በቤት ውስጥ ይከወን የነበረው የምርት ሂደት ማሽኖች ካፒታልና የሰው ጉልበት ተሰባስበው ወደሚገኙባቸው የማምረቻ ትክሎች እንዲሻገሩ ሲደረግ ለቴክኖሎጂዎች በየአይነታቸው መልማትና መበልጸግ ምክንያት ሆኗል። ይህ እንቅሳቃሴ ነው እንግዲህ ለኢንዱስትሪው አብዮት ጅማሮ እርሾ ሆኖ የነበረው። አብዮቱ በተራው ለሌሎች ቴክኖሎጂዎች በስፋትና በብዛት መልማትና ጥቅም ላይ መዋል አቀጣጣይ ሆነ።
ይህ ከመሆኑ ሺዎች ዓመታት ቀደም ብሎ የግብርናው አብዮት ተከስቶ ነበር።  የግብርናው አብዮት የእኛንና መሰል አገሮች በኩል ማለፉን የሚያሳይ ምልክት የለም። እርግጥ እንደ አገር አልፎን የሄደ አብዮት ይህ ብቻ አይደለም። የአስራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮትና የሀያኛው ክፍለ ዘመን ዲጂታል አብዮትም እንዲሁ መኖራችንን ሳያውቁ ወይም ለመኖራችን እውቅና ሳይሰጡ ነው የተከሰቱት በየአገሩ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ቴክኖሎጂን በስፋት የመጠቀማችን ያህል የህዝብ ብዛት እየጨመረ መምጣትና ለቴክኖሎጂው ግብአት የሆኑት የተፈጥሮ ሀብቶች (ለምሳሌ ማዕድናት) መጠን ውሱን መሆን አንድምታው መልካም አይደለም። የምድራችን ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት ግብአት የሚሆነው ጥሬ ዕቃ የማቀበል አቅም ሆነ የተወሰነ ነው።  ተጠቅመን የምንጠለውንና የምንልቀውን ብክለት የማርከስ አቅሟም እንዲሁ የሰው ልጅ ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ ከሚመጣው አባካኝ የእድገት ጉዞ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ አይደለም።  ለዚህም ነው በረከቱን ከመርገም እያበራየ የሚለይ አሰራርና አካሄድ አስፈላጊ የሚሆነው።
የቴክኖሎጂ ችግር የሚያያዘው ከምናውቃቸው ተጽእኖዎች ጋር ብቻ አይደለም። ዛሬ በጎ፤ ተጽእኖ አልባ እንዲያውም ችግር ፈቺና ‘ምትኩ’ ብለን ያመጣነው ቴክኖሎጂና ውጤቱ ከዓመታትና ከአሰርተ ዓመታት በኋላ ጠንቀኛና መዘዘኛ ሆኖ እናገኘዋለን። እዚህ ላይ ዲዲቲን ማንሳት ይቻላል። ዲዲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈረከበበት ወቅት እንደ ‘ህይወት አድን’ ኬሚካልነቱ ስለ በጎነቱ ብዙ ተብሎለት ነበር።ነጩ የዲዲቲ ዱቄም ከቤት ውስጥ እስከ ውጪ ያለ ምንም ገደብ በስፋት ተረጭቷል። ለዓመታት እንዲህ ነግሦ ከተቀጠለ በኋላ ነው እንግዲህ የዲዲቲ የጎንዮሽ ጉዳቱ በጣም እንዲሚከፋ የተረዳነው ወይም መረዳታችን ይፋ የሆነው።  ከኦዞን ንጣፍ መሳሳት ጋር ተያይዞ ስማቸው የሚነሱት ኬሚካሎችም ቢሆኑ አንዱ አስቸጋሪ ኬሚካል ከገበያ አውጥተን በሌላ አዲስ ከመተካቱ ነው አዲሱ ኬሚካል ባለ ሌላ ችግር መሆኑን እየታወቀ የመጣው።
ለእንደዚህ አይነት ችግርን በችግር የመተካት ሂደት ዋነኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የዕውቀታችን መጠን ውሱን መሆን ነው። አዎ በአንድ ጊዜ በአንድ ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ውጤት ምክንያት በአጭርና በረጅም ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ  ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለማወቅ አልተቻለንም - አንዱን ጥለን አንዱን አንጠልጥለን ፤ አንዱን አጉልተን ሌላውን አላልተን ከመሄድ ውጪ።
በአቅም ማነስ ምክንያት ከሚደረገው የጎዶሎ እይታ አካሄድ ይበልጥ ዓለምን ወደ ማይሆን መንገድ እየወሰዳት ያለው ይህንን ከፊል እይታ እንጂ ሙሉ እይታን ሊፈጠር የማይችለው አሰራራችን ነው። ለምሳሌ የከፍተኛ ትምህርት አሰጣጥና የምርምር መዋቅራችን እያንዳንዱ ዘርፍ የሚተያይ እንጂ የማይገናኝ መስመር ይዞ በየራሱ የሚፈስ ነው። በአብሮ መስራት ስም ቢጠጋጉም እንኳን መቼም ቢሆኑ እንደማይገኛኙት ትይዩ መስመሮች ሳይገናኙ ይሰራሉ ሳይገናኙ መፍትሔ ልስጥ ይላሉ። በእንደዚህ አይነት የትምህርት ስርአት የሚገኙ ምሁራንም በተለያየ መስክ ባለነጭ ኮሌታም ባለሰማያዊ ኮሌታ ሆነው ሲሰማሩም የሚያስቡት የሚሰሩትና የሚያሰሩትም ሙሉ ገጽ የሌለው የተከፈለ ስራ ነው።
በተመሳሳይ ከፍሎ ማየት ብቻ የሚያስችል የምርምር መሰረተ ልማትና ስርአት የሚያበለጽጋቸው ቴክኖሎጂዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶችም የሚያመጡት በጎ ነገር የተከፈለ፤ የሚፈቱት ችግርም የተከፈለ ቢሆን ባህሪያዊ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ለመንቀል በሚያስቸግር ደረጃ በስፋትና በጥልቀት ስር ሰደው የሚገኙ የተለያዩ የምጣኔ ሀብቶቻችን መሰረተ ልማቶች ከነችግሮቻቸው ባሉበት ለመተው የተገደድነው ገና ሲጀመር በሙሉ እይታ አስበን ያልዘረጋናቸው  በመሆኑ ነው። የነበሩትን ባሉበት ቦታ ስናስፋፋቸውም ከጥንቱ ከመሰረቱ በነበረው እሳቤ አኳያ ነው። በሌሎች ቦታዎች እንደ አዲስ ስንዘረጋ ሳይቀር በዛው እንደዛው አድርገን ነው። ለምሳሌ የከተሞች የውኃ አቅርቦት አገልግሎትን ማየት ይቻላል - በአዲስ አበባችንም በሌሎች የበለጸጉ አገሮች ከተሞችም አሁን ድረስ ያለው ነገር። ወደየቤታችን የሚመጣው የውኃ መስመር አንድ ሲሆን ውኃውን የምንጠቀምበት ግን ለተለያየ ነገር ነው - ለመጠጣት፤ ለማብሰል፤ ለማጠብና ለመታጠብ፤ አትክልት ለማጠጣትና ለሽንት ቤት መቸለሻ። ለነዚህ የተለያዩ ጉዳዮች የምንጠቀምበት ውኃ ጥራት ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ነው። በአዲስ አበባ ከለገዳዲ ወይም ከለገጣፎ ወይም ከአቃቂ በኤሌክትሪክ ኃይል እርዳታ የሚጓጓዘው፤ ኪሜካሎችን በመጠቀምና ብዙ ወጪ ወጥቶበት ለመጠጥ በሚሆን ደረጃ የታከመና በየመንገዱ ከሚባክኑት ወገኖቹ ተለይቶ በለስ ቀንቶት ከቤታችን ከደረሰው ውኃ ቀላል መጠን የሌለውን ለሽንት ቤት መቸለሻ አድርገነው ቁጭ።  እንዴት ለመጠጥም ለሽንት ቤት መቸለሻም የሚሆን ውኃ እኩል ይታከማል? ለምን እኩል ርቀት ይጓጓዛል? እንዴት እኩል ወጪ ይወጣበታል? ለምን እኩል ለብክነት ይጋለጣል? እነዚህ ጥያቄዎች በዲሲም በደሴም መልስ ያላገኘንላቸው ጥያቄዎች ናቸው።
ወደፊት በሚመጣው ትውልድ አይን ‘ምን ነክቷቸው ነበር እንደዛ እንጂ እንዲህ ያላሰቡት?’  ተብለን ከምንጠየቅባቸው ብዙ ነገሮች መካከል አንዱ ይሄ መሆኑ አይቀርም።   
 እርግጥ ነው በተናጠል የሚደረጉ የቴክኖሎጂ ተጽእኖ ግምገማዎች ነበሩ፤ አሉም።  ለምሳሌ በ’ነበሩ’ነት ከሚጠሩት መካከል የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ግምገማ ጽ/ቤት ማንሳት ይቻላል። የቴክኖሎጂ ግምገማ በይፋና ተቋማዊ ቅርጽ ተሰጥቶት የተጀመረው ይህ ጽ/ቤት የዛሬ አርባ ዓመት ሲቋቋም ነበር። ምንም እንኳን በግምገማ ስራው ሁለንተናዊ ጥናት ለማድረግ ቢሞክርም ሙሉ እይታ ግን አልነበረውም - በተለይ የረጅም ጊዜ ተጽእኖዎችን ከመቅለብ አኳያ። እንደዛም ሆኖ ይህ ጽ/ቤት ከሃያ ዓመታት በላይ ከሰራ በኋላ እንዲዘጋ ተደርጓል።
ወደ አገራችን ስንመለስ በበረከትነት የሚቆጠሩ ለውጦች እየታዩ ነው - በተለይ በመሰረተ ልማት ዝርጋታው። በዛው ልክ የኑሮው ውድነት በጣም የመታቸው ወገኖች ቁጥር ከፍተኛ ነው። በአንድ በኩል ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዓመታዊ የአባልነት ክፍያ በአስራ ምናምን ሺዎች ብር የሚያስከፍሉ አሉ - የሚከፍሉ ስላሉ።  በሌላ በኩል በልቶ ለማደር የተቸገረ ወገንም አለ። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው ውሳኔ ሰጪ አካላት በረከቱ ከመርገም ጋር ሳይያያዝና ሳይነካካ እንዲስፋፋ መጣር ያለባቸው። ውሳኔ ተቀብለን የምናስፈጽመው አዳሜና ሔዋኔም እንዲሁ የየድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል። በረከት ይትረፍረፍ መርገም ይረፍረፍ!አሜን።

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: