Sunday, November 25, 2012

የህልም መስመረኛ


(ጌታቸው አሰፋ፤ መስከረም 18  ቀን  2004 ዓ.ም.) በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራ የሚያደርጉኝ ብዙ በርካታ ነገሮች አሉ። አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው (አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ ያየሁት የአስተናጋጆቹ ለራሳቸው አገር ሰው ያላቸው ከተገቢ በታችና አሳፋሪ መስተንግዶና አያያዝ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው)። የዛሬ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ስለ ኩራት እንጂ ስለ ሀፍረት አይደለም። አየር መንገዳችን ከዘመን ዘመን በተሻገረ ቁጥር ከእድገት ወደ እድገት የሚሸጋገር፤ ማለም የማያቆም፤ አልሞም የሚፈጽም፤ በአቻነት መነጋገር፤ በአብሮነት መስራት የሚችል፤ለሌሎች አገሮች የሚተርፍ አቅም የገነባ ነው - ደስ ሲል። በቅርቡ ድሪምላይነር (የህልም መስመረኛ) ተብሎ የሚታወቀውን ዘመናዊውን ቦይንግ 787 አውሮፕላን ገዝቶ በመረከብ ከዓለም አየር መንገዶች ሦስተኛ ሲሆን፤ በአገር ደረጃ ደግሞ ከጃፓን ቀጥሎ አገራችን ሁለተኛ ሆናለች።

ባለፈው ሳምንት የምርትና የአገልግሎት ዲዛይን ኡደታዊ የአካባቢ ተጽእኖ ላይ የሚተኩረውን ትምህርት ማስተማር ስጀምር በምሳሌነት ካቀርብኳቸው የምርት አይነቶች አንዱ ይሄው የኢትዮጵያ አየር መንገዱን 787 አውሮፕላን ነበር።  ለመሆኑ ቦይንግ 787 ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድነው? ቦይንግ 787 ሁለት አይነት ሲሆን አንዱ ቦይንግ 787-8 ፤ ሁለተኛው ደግሞ ቦይንግ 787-9 ተብሎ ይጠራል። የሁለቱ ልዩነት በዋናነት በመጠን ሲሆን ከዛ ጋር ተያይዘው በሚመጡ ነገሮችም ነው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ የተረከበው ቦይንግ 787-8ን ነው። 787-8 ከ234 እስከ 296  የሚደርሱ መንገደኞችን ማሳፈር እንዲችል ተደርጎ የሚሰራ  ሲሆን  የአየር መንገዳችን ባለ 270 መቀመጫው ነው።
ጥቅም ላይ የዋሉት ሞተሮችና የተሰራበት የዕቃ አይነት አውሮፕላኑ በመጠን ከሚመስሉት ሌሎች አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸር ወደ ሃያ ፐርሰንት የነዳጅ ፍጆታ ቅነሳ እንዲኖረው አድርገዋል። ይህ ያነሰ የነዳጅ ፍጆታ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው።  ለአየር መንገዱ ትርፋማነት መጨመር፤ ነዳጅን ከውጭ በውጭ ምንዛሪ ለምታሰገባው ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ቁጠባ እንዲሁም ለዓለማችን የአካባቢ አየር ብክለት (የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ)  ቅነሳ  አስተዋጽኦ አለው።
እስካሁን ያሉት አውሮፕላኖች ዋናው አካላቸው የሚሰራው ወደ 50,000 ማያያዣዎችን በመጠቀም ከተለያዩ የአልሚኑየም ንጣፎች ነበር። ቦይንግ 787ን ልዩ የሚያደርገውና የአውሮፕላኑን ክብደት በመቀነስ  የነዳጅ ፎጆታውንም በመጠን እንዲያንስ የሚያደርገው ቀለል ካለ አዲስ ድብልቅ ቁስ መሰራቱ ነው። ይህ ቀላል ቁስ የተሰራው ከካርቦን ክሮች ነው። ከዚህ ቁስ በተጨማሪ ሁለት ነዳጅ ቆጣቢ አዳዲስ የሞተር አይነቶች ጥቅም ላይ የዋለበት ነው - ቦይንግ 787።አውሮፕላኑ አየሩን እየቀዘፈ በቀላሉ እንዲሄድ የሚያደርገው ስምሙ ዲዛይንና ተጨማሪ ቴክኖሎጂዎች ነዳጅ ቆጣቢነቱ ላይ በጎ አስተዋጽኦ አድረገዋል። አየር መንገዳችን ነሐሴ ላይ የተረከበውንና በአሁኑ ሰዓት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመብረር ላይ የሚገኘው እስከ 200 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣውን 787 ሌሎች ዘጠኝ እሱን መሰል አውሮፕላኖች አንድ በአንድ ይቀላቀሉታል ተብሎ ይጠበቃል።
የዚህ አውሮፕላን ግንባታም እንደ ሌሎች የቦይንግ አውሮፕላኖች በአሜሪካ የተካሄደ ቢሆንም ከሌሎች በተለየ መልኩ ሙሉ በሙሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ አንድ ቦታ ላይ ተሰርቶ እንዲያልቅ ተደርጎ አይደለም የተሰራው። ያለቀላቸው የሚባሉ የተለያዩ የአውሮፕላኑ ክፍለ-አካላት በተለያዩ አገሮች በሚገኙ ኩባንያዎች ተገንብተው የመጡ ሲሆን ከ800 እስከ 1,200 የሚደርስ የሰው ኃይል በመጠቀም እነሱን አንድ ላይ መግጠምና ከዛም ከሌሎች የቴክኖሎጂ ስርአቶች ጋር ማዋሃድ የተሰራው ግን በዋሽንግተን ግዛት በሚገኘው የቦይንግ ማምረቻ ጣቢያ ነው። ይህ አሰራር ቀልጣፋና ሦስት ቀን ብቻ የሚፈጅ የመጨረሻ ገጠማ ስራ እንዲኖረው አድርጎታል።
ክፍለ-አካላት በመስራት የተሳተፉት  የጃፓን፤ ጣልያን፤ ደቡብ ኮሪያ፤ አሜሪካ፤ ፈረንሳይ፤ ህንድ፤ እንግሊዝ እና ስዊድን ኩባንያዎች ናቸው። ከነዚህ ሁሉ ግን የጎላ ሚና የጃፓን ኪባንያዎችን እስከ 35 ፐርሰንት የሚደርስ የሥራ ድርሻ በመውሰድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል። ቦይንግ ከዋሽንግተኑ በተጨማሪ በሳውዝ ካሮላይናም ሌላ አዲስ መገጣጠሚያ አለው። ቦይንግ ኩባንያ ለ787  የሚሆኑ ለክፍለ አካላት ማጓጓዣ ይሆኑ ዘንድ ከአሁን በፊት ያገለገሉ አራት 747-400s አውሮፕላኖችን ውስጣቸውን በመቀየር ለዚህ ስራ ተጠቅሞባቸዋል።
ቦይንግ 787 ድምጽን በመቀነስ በኩልም እስከ ስድሳ ፐርሰንት የሚደርስ ማሻሻያ አድርጓል። አየር መንገዳችን ሁለተኛውን  ቦይንግ 787 አውሮፕላን መስከረም ላይ ሦስተኛውን ጥቅምት፤ አራተኛውን ኅዳር ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።
የመጀመሪያውን አውሮፕላን ለመረከብ የተለያየ መዘግየት ከመፈጠሩ አንጻር አሁንም መዝግየት የማጋጠም እድል ይኖራል። ይህ መዘግየት በራሱ በቦይንግ እቅድም የተንጸባረቀ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቦይንግ 787 እ.አ.አ.  ሜይ 2008 ይጀምራል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው በረራ የተደረገው ግን ዲሴምበር 15, 2009፤ በመደበኛ የበረራ መስመር የገባው ደግሞ በኦክቶበር 26, 2011 ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቦይንግ 787 በመረከብ ከቀደሙት ሁለት የጃፓን አየር መንገዶችን አንዱ የሆነው ኦል ኒፖን ኤርዌይስ  ሌላም ከአካባቢና ኃይል አጠቃቀም አኳያ ጠቃሚ የሚባል በረራ በቦይንግ 787 ፈጽሞ ነበር።
ይህ ሰላማዊ ውቅያኖስን አቋርጦ የሄደው በረራ ሊከናወን የቻለው መደበኛውን የጄት ነዳጅን ጥቅም ላይ ከዋለ የምግብ ዘይት በተሰራ ነዳጃ ጋር በመቀላቀል ነው። ይህ በረራ አንድ አይነት መጠን ካላቸው መደበኛ አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸር ወደ ሰላሳ ፐርሰንት የልቀት መጠን ቅነሳ ነበረው ተብሎ ተገምቷል። ከላይ እንደተመለከትነው ወደ ሃያ ፐርሰንቱ ቅነሳ የሚያያዘው ከአውሮፕላኑ ስሪት ጋር ሲሆን ቀሪው አስር ፐርሰንት ደግሞ በዚህ በረራ ወቅት ላይ ጥቅም ከዋለው ነዳጅ ነው።
ከዚህ ታሪካዊ በረራ በፊት ሰኔ 2003 ዓ.ም. ቦይንግ አዲሱ 747-8 እቃ ጫን ግዙፍ አውሮፕላን ወደ አስራ አምስት ፐርሰንት ያህል ለወትሮው ለእንስሳት መኖ መስሪያ ከሚሆን እጽ ከተመረተ ነዳጅ ከመደበኛው ጄት ጋር በማደባለቅ አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ እንዲሄድ ተደርጎ ነበር።  ቦይንግ የተለያዩ የ787 አይነቶች ለመስራት እቅድ ያለው ሲሆን ከእነዚህም መካከልም እቃ ጫኞችን ይጨምራል። ከዚህ በተጨማሪ  ኤር ፎርስ ዋን ተብሎ የሚተወቀውንና የአሜሪካ ፕረዚደንቶች መጓጓዣ ተብሎ የሚሰራውን አውሮፕላን አሁን ያለውን ቦይንግ 747 ላይ ተመስርቶ የተሰራውን በቦይንግ 787 ለመተካት እቅድ ይዟል።
በኩራት የተጀመረው ጽሁፍ በኩራት ወደ ማለቁ ቢጠጋስ?የዓለም ኢኮኖሚ - ያደጉት አገሮች ሳይቀር - ጥግ ይዞ በሚቆዝምበት በአሁኑ ወቅት ለቦይንግ 787 መግዣ ለአየር መንገዳችን ወደ አንድ ቢልዮን ደላር የብድር ድጋፍ የሰጠው JP Morgan የአውሮፓ፤ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ የንግድ ፋይናናንስ ቢዝነስ ኃላፊ እንደተናገሩት በአስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን ይህን ያህል ገንዘብ እንዲያበደሩ ያደረጋቸው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ ያላቸው አመኔታ ነው። የአሜሪካ የወጪና የገቢ ንግድ ባንክ እስከ 85 ፐርሰንት የሚያህል የአውሮፕላኑን ወጪ ይሸፍናል። አመኔታን የመሰለ የኩራት ምንጭ ከየት ይመጣል? በመጨረሻም በአገራችንና በዓለማችን ዙሪያ ከኃይልና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚያያዙ ዋና ዋና ክስተቶች መካከል ለጥቂቶቹ’ ✓ እና X’ እንሰጣለን። አዳማ 1 የነፋስ ኃይል ማመንጫ ስራ የጀመረው በዚህ ሳምንት ነው። ባለ 51 ሜጋዋቱ የኃይል ማመንጫ  ወደ 117 ሚልዮን ዶላር ወጪ ያስወጣ ሲሆን አገሪቱ አላት ከሚባለው  1000 000 ሜጋዋት የነፋስ ኃይል የማመንጨት አቅም ውስጥ ጥቅም ላይ በመዋል ሁለተኛው  መሆኑ ነው-✓። ለአገራችን የአረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ግንባታ የሚውል 7.5 ቢሊዮን ዶላር ለመሰበስብና ስራዎችን ለመደግፍ እንደ ገንዘብ ቋት የሚያገለግል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የገንዘብ ተቋም ተመስርቷል-✓። እያለቀ ባለው በጋ ወቅት የተስተዋለው የግሪንላንድ፤ የአንትራክቲክን እና የአርክቲክ ግግር በረዶዎች ሳይንሳዊ ጥናቶች አስቀድመው ከተነበዩት በበለጠ ፍጥነት መቅለጥ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል። ይህም የአየር ንብረት ለውጥን በማባባስና የባህር ጠለል ቀላል በጣም ከፍ እንዲል በማድረግ የባህር ዳርቻ ከተሞችንና አገሮችን ስጋት ላይ ይጥላል-X።
=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: