Sunday, November 25, 2012

ክረምትና በጋ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ነሐሴ 19  ቀን  2004 ዓ.ም.) የአገራችን የደንና አረንጓዴ ሽፋን ጉዳይ ክረምት ክረምት ሲታይ አማን ይመስላል።  ለወትሮው ራሰ በራ የሚመስለው የሰሜኑ ሜዳና ሸንተረርም ሳይቀር በስሱም ቢሆን በአረንጓዴ ቀለም የተቀባ እንዲመስል የሚያደረገው ክረምት ነው።  ክረምት ከበጋ አገር ምድሩ ሁሉ አረንጓዴ ማድረግ እንኳን ባይቻል እና ባይጠበቅም ቢያንስ ትንሽ የማይባል የአገሪቱ ክፍል ወጥ የሆነ የደንና የሌላ አረንጓዴ ሽፋን እንዳይኖረው የሚደረግበት ምክንያት ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ውኃና አልሚዎችን እስካለን ድረስ ይቻላል።

ውኃ
ድሮ ድሮ የክፍለሀገር ልጅ መሆን ራሱ ከሞላ ጎደል ዋና ለማስቻል በቂ ነበር። ለምን ቢባል አነሰም በዛም በአካባቢው ወንዝ ስለሚኖር እዛ በመለማመድ ስለሚጀምር። ድሮ ድሮ ድሮ ደግሞ አዲስ አበባም እንደዛ ነበር። ምክንያቱም እዛም ይዋኝ ስለነበር። አሁን የአዲስ አበባዎ ወንዞች ለመዋኘት ቀርቶ በአጠገባቸውም ለማለፍ አይመቼ ከሆኑ ውለው አድረዋል።  በአብዛኛው በብክለት ምክንያት ነው። ይህ ብክለት ክረምት ክረምት የሚጎርፈው ጎርፍ እንኳን ማጽዳት ከሚችለው በላይ ነው።
ዛሬ ዛሬ ግን የክፍለ ሀገር ከተማም ሆነ ገጠር ወይም አዲስ አበባ በተለይ በበጋው ለመዋኛ የሚሆን ውሃ ብቻ ሳይሆን ለምልክት የሚሆን ውሃ የሌላቸው የቀድሞ ወንዞች አሉ። የቀድሞ ወንዞች የቀድሞ ሃይቆች የቀድሞ ኩሬዎች የቀድሞ ምንጮች ወዘተ በየመንደሩ በየሰፈሩ በየከተማው በየገጠሩ አሉ። ወደ ቀድሞነት የተዛወሩት እነዚህ ውኃማ አካላት ለዚህ ያበቃቸው ከገጸ ምድራዊም ከከርሰ ምድራዊ ምንጫቸው አካባቢ የሚገኘውን እርጠበት አቅቦ የሚያቆይ አረንጓዴ ሽፋን ባለመኖሩ ምክንያት ነው። ‘ላለው ሁሉ ይጨመርለታል’ እንዲል መጽሐፍ በእጁ ያለውን እርጠበት የተንከባከበ ሌላም ያገኛል። በአንድ ቦታ ያለን የላይኛው የአፈር ክፍል እርጠበትም ሆነ በከርሰ ምድር መጋዘን ውስጥ ያለውን ውኃ ሚዛኑን ጠብቆ ካልሄደ የሚፈስ የወንዝ ውኃም ሆነ የሚንፈላስ የሐይቅ ውኃ ቀጣይ ህልውናቸው አጠራጣሪ ነው የሚሆነው። ውኃ እንዳይኖር የደኖች መጨፍጨፍ ምክንያት የመሆኑን ያህል ውኃ ባለመኖሩ ደግሞ የደንም ሆነ የሌሎች እጽዋት ሽፋንም ቢያንስ በበጋ እንዳይኖር አድርጎታል።
በአገራችን እንዲኖረን የምንፈልገው ወይም በተጨባጭ ያለውን የሰውና የእንስሳት ብዛት ግምት ውስጥ ያስገባ የውኃ አቅርቦት እንደሚያስፈልገን ሁሉ ከዓመት እስከ ዓመት የሚቀጥል ለምለም ንጣፍ እንዲኖረን የሚያስችል የውኃ በጀት ያስፈልጋል። የመንግሥት የፋይናንስ በጀት ለቋሚ ነገሮችና ለስራ ማስኬጃ ተብሎ በሁለት ዋና ዋና አቢይ ርዕሶች እንደሚከፈለው ሁሉ ውኃችንም በቋሚነት ለስነምህዳራዊ አገልግሎት ለምንፈልጋቸው ደኖች ልማትና ለኢኮኖሚያችን በሰውና በእንስሳት በኩል ግብአት ለሚሆኑን ምርቶች ማምረቻ እንዲሆኑ ለምፈልጋቸው ተክሎችና ሌሎች እጽዋት ማልሚያ የሚያስፈልገንን በሚያጠቃልል መልኩ ‘መበጀት’ አለበት። 
ስንት ውኃ የት አለን? ማወቅ አለብን። በወቅት ሲከፋፈልስ ምን ይመስላል? በእርጥብ ዓመትና በድርቅ ዓመትስ ከቦታ ቦታ ያለው ልዩነት ምን ይመስላል?ወዘተ ማወቅ ጠቃሚ ነው።
በምኖርበት ህንጻ በዚህ ሳምንት በጥገና ምክንያት ውኃ ለሦስት ቀናት ያህል በዚህ በዚህ ሰዓት አይኖርም ተብሎ አስቀድሞ በጽሁፍ ተነግሮን ነበር። እናም የውኃ አልባ ሰዓታት የመጀመሪያው ቀን ደረሰ። ምሳ ሰዓት አካባቢ በቤት ውስጥ ያለው የውኃ መጠን ወደማስበ የሚያስገባ ሁኔታ ተፈጠረ። በቤቱ ውስጥ ያለነው አዋቂዎች ለወትሮው  የምንጠጣው ከቧንቧ ውኃ ነው። በምዕራቡ ዓለም ቀጥታ ከቧንቧ ተቀድቶ የሚጠጣ ውኃ የሚያቀርቡ ከተሞች ሁሉም አይደሉምና እዚህ መቻሉ ተመስገን ነው። የታሸገ የሚጠጣ ውኃ የምንገዛው  ለሕጻን ልጃችን ብቻ ነው። እናም በቤቱ ያለው  ለሱ ተብሎ የተገዛው የታሸገ ውኃ ለምን ለምን መጠቀም እንደምችል ማሰብ ጀመርኩ።  ፓስታ ለምሳ ለመስራት ውኃ ያስፈልገኛል። ሽንት ቤት ለመቸለሻም የተወሰነ ውኃ።  እቃ ለማጠብና ለመጠጣትም እንዲሁ። የታሸገው ውኃ ብቻ ነው ለዚህ ሁሉ። ባለፈው ጽሑፍ እንዳነሳሁትና ከዛም በባሰ የታሸገ ውኃ ለሽንት ቤት መቸለሻ መጠቀም ከኢኮኖሚ፤ ከአካባቢና ከማኅበራዊ አገባብ አንጻር ደስ የማይል ነው። እናም ቅር አለኝ። በመደበኛነትና በነጻ የሚገኝ ውኃን መጠቀም ቅር አያሰኝም። በበጀት አስተሳሰብና አሰራር መሰረት ‘ስንት አለኝ? ለምን ለምን ላውለው?’ በሚል አሰራር መመራት ግን ያለን ሀብት ውሱንነት ከፊታችን ድቅን ከማድረጉም በላይ ሀብቱን በአገባቡ ለማልማትና ከሱ የምናገኘውን አገልግሎት ለማሳደግ እንለፋለን።
ባለፈው በፎቶው ባለሙያ ቢንያም መንገሻ ቀርቦ የነበረው የፎቶ አውደ ርእይ ላይ ተካተው ከነበሩት ፎቶዎች መካከል አንዱ በቀጭኑ የሚፈስ የሆነ ፏፏቴን የሚያሳይ ነበር። ውኃው ድፍርስ ነው። ከፏፏቴው ራስጌ ከሚገኘው የወንዝ ክፍል ሁለቱም ዳርቻ በካሜራው አይን የተሸፈነው ያህል ሲታይ አረንጓዴ ልብስ ተከናንቧል። ከፎቶው ስራ ፏፏቴው የትኛው እንደሆነ መቼና እንደተነሳም አይናገርም። እናም መገመት ብቻ ነበር የምንችለው - ቢያንስ ቢንያምን አግኝተን እስክንጠይቀው። እናም ገመትን። እኔ አብረውኝ ለነበሩት ግምቴን ‘በመረጃ የተደገፈ’ አይነት ለማድረግ ሞከርኩ። ‘ጢስ አባይ ሊሆን አይችልም!’ አልኩ። ለምን ቢባል ውኃው ድፍርስ መሆኑና ዙሪያ ገባው ለምለም መሆኑ ፎቶው የተነሳው ክረምት ላይ መሆኑን ያሳያል። ጢስ አባይ ደግሞ በክረምት በቀጭኑ የሚፈስ ፏፏቴ ሳይሆን የሚንፏፏበት አልጋ ከጫፍ እስከ ጫፍ ግጥም አድርጎ ሞልቶ የሚፈስ ነው።”  ብዬ አስረዳሁ። ይመኑኝ ወይም ይሁንልህ ይበሉኝ ብቻ ማብራሪያዬን የተቀበሉኝ መስሎኝ ነበር። ይሁንና ትንሽ እንደቆየን ቢንያም ስለዛ ፎቶ ግራፍ ሲናገር ፎቶው የጢስ አባይ መሆኑ ሰማሁ። ትላንት ከትላንት ወዲያ ይሰራ የነበረ ትንተና ዛሬ አልሰራም። ምን ያህል የውኃ መጠን ከየት ተነስቶ የትና መቼ ይሄድ እንደነበር ማወቅ ማለት ዛሬ ምን ያህል ውኃ የትና መቼ እንደሚሆድ ማወቅ ማለት አለመሆኑን እንዳስታውስ የተደረግኩበት አጋጣሚ ነበር።    
አልሚዎች
ስለ ውኃ በማንሳት ጀመርኩ እንጂ ለአረንጓዴ ሽፋን የሚያስፈልገው ውኃ ብቻ ነው ማለቴ አይደለም። አፈሩ ከአልሚ ንጥረ ነገሮች የተራቆተ መሆን የለበትም። እንደ እጽዋቱ አይነት የሚያስፈልገው አቢይና ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች በበቂ መጠንና በተፈላጊው አይነት መገኘት አለባቸው። እነዚህ አልሚ ንጥረ ነገሮች ደግሞ በመጠን ውሱን ከመሆናቸው አንጻር አላቂ መሆናቸው ነው ችግሩ። ለብዙ ሺህ ዘመናት ሰው የኖረባቸውና የተጠቀማባቸው የደጋው ኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይ በሰሜኑ ክፍል የሚገኙት ቦታዎች ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች የመራቆታቸው ማብራሪያ ያለው ቦታዎቹ ያለምንም የመተካት ወይም መልሶ የመጠቀም ስራ አልሚዎችን እንደወጡ እንዲቀሩ በሚያደርግ አሰራር ለዘመናት ከመነጨታቸው ላይ ነው። የእንግሊዝ አፍ ተናጋሪዎች ዘንድ ‘ኬክህን በአንድ ጊዜ ልትበላውና ልታስቀምጠው አትችልም’ የሚል አባባል አለ። ‘ከበላኸው የለም፤ ካለ አለበላኸውም’ ማለታቸው ነው። በየቦታው በየስፍራው ከሚገኘው የአገሪቱ አፈር ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር  ያልበላነው ነው። የበላነው የለም። ከኬኩ በተለየ እየበላን ማኖር የምንችልበት ሁኔታ ግን መፍጠር እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ከየአፈሩ በየእጽዋቱ አማካይነት የሚወሰደው አልሚ ንጥረ ነገር በአብዛኛው ተመልሶ ወደመጣበት አፈር አስቀድሞ በታሰበበት አሰራርና መጠን እንዲመለስ የሚያደረግ አሰራር መደበኛ እንዲሆን ማስቻል ይጠይቃል።  
እዚህም ላይ የበጀቱ ጉዳይ እንደማሳያነት ጥቅም ይሰጣል። ምን ያህል ንጥረ ነገር የት ቦታ በምን ያህል ጥልቀት አለን? የመጠኑና የአይነቱ መለያየት ከወቅቶች መፈራረቅ  ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል? እነዚህና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው። የውኃና የአልሚ ንጥረ ነገሮች ባንኮቻችን ውስጥ ያለን ሂሳብ ምን አይነት ነው? ዝግ ሂሳብ ነው? በየጊዜው የሚወልድ ቆጣቢ ሂሳብ ነው? ወይስ ዝግም ያልሆነ የማይወልድና በአንድ ወቅት ብቻ የነበረውን ገንዘብ እያወጣን እንድናጠፋው የሚያደርገን ሂሳብ?   
ከሂሳቡ አይነት ጀምሮ በምን ያህል መጠን ጥቅም ላይ ይዋል? በምን ይህል መጠንስ ይውለድ የሚለውን እስከመወሰን ድረስ እንደ አገር የአንበሳውን ድርሻ በእጃችን ነው።  
 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: