Sunday, November 25, 2012

ይድረስ ለመንግሥት- ሞያ በልብም በግልጽነትም ነው።


(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥቅምት 23  ቀን  2004 ዓ.ም.)እነሆ አባያችንን ለመደገብ የተጀመረው ታላቅ ፕሮጄክት ደጋፊም ነቃፊም የሚለውን እያለ ባሳለፈበትና ባለበት ሁኔታ ከአስር በላይ ወይም በትክክል ለመግለጽ አስራ አንድ ፐርሰንት ያህሉ መጠናቀቁን መንግሥት እየተናገረ ነው። በሀዘንም በደስታም ምክንያት ለአንድም ቀን ቢሆን ስራው ሳይቋረጥ እየቀጠለ መሆኑን ተነግሮናልና - ደስ ይላል። ደስታችንን እያጣጣምን መነሳት ያለበትን እናነሳለን።
ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ‘የፈለገው ነገር ቢመጣ አባይን ገድቦ ከመጠቀም የሚያግደኝ ኃይል የለም’ ብላ ስራውን የጀመረችው ለዘመናት የነበረውን ምኞት እውን እንዳይሆን ሲያስፈልግ በወታደራዊ ጡንቻ፤ ሳይሆን በዲፕሎማሲና የገንዘብ ምንጮችን በማድረቅ የነበረውን እንቅፋት ሁሉ ለማስወገድ በጓዳም በአደባባይም ስራዎችን ስትሰራ ከቆየች በኋላ ነው።
እነ ግብጽን ለማለዘብ ባለ ብዙ መስመር አካሄድ ስትከተል ቆይታ ስታበቃ ነው ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የገባችው።  ግንባታው ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ሱዳንና ምድረ-ፈርዖን ግብጽ መቼም ቢሆን ፕሮጂክቱን በበጎ ባያዩትም እንኳን እንደ አጥፊያቸው እንዳያዩት ግን ከመንገዷ ወጥታ እነሱ  ከአባይ ያገኙት የነበረው የውኃ መጠንን እንደማይቀንስ ለማረጋገጥ ራሷ ካደረገችው ጥናት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ የተውጣጡ ስድስት ባለሞያዎች እንዲሁም አራት ሌሎች ዓለም አቀፍ ባለሞያዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እንዲያካሂድ ሃሳብ አቅርባ እየተፈጸመ ይገኛል። ይህ ዓለም አቀፍ የባለሞያዎች ቡድን ስራውን በይፋ የጀመረው ግንቦት 7 2004 ሲሆን በዛው ወር የግንባታ ቦታው ድረስ በመሄድ ጎብኝቶ ነበር። ከአምስት ወር በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ አሁን በቅርቡ ቦታውን ጎብኝተዋል።
የመጨረሻ ሪፖርታቸውን የካቲት ላይ ያወጣሉም እየተባለ ነው። ከዚህ ቡድን የምንጠብቀው ምንድነው?  መረጃ አሰባሰባቸው እንዴት ነው? በየስብሰባቸው ውሳኔ ወደ መስጠት ሲሄዱ እንዴት ነው ውሳኔ የሚወስኑት? የመጨረሻው ሪፖርት እንዴት ነው የሚዘጋጀው? እንዴትስ ነው የሚቀርበው? የማንፈልገው ውጤት ይዞ ከወጣስ እንዴት ነው የሚሆነው? የቡድኑ ውጤት ምንም ይሁን ምን፤ ተፈላጊም ይሁን የማይፈለግ ተጽእኖ የማሳደር እድሉ ምን ያህል ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚጠበቀው ከመንግሥት ነው። መንግሥት ለህዝብ ሂደቱን በሙሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በግልጽ ማሳወቅ አለበት። እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ አስፈላጊ የሚሆነው ያለፈው ልምዳችንን ግንዛቤ ውስጥ አካተን ስንመለከት ነው።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ገምጋሚዎችና ዓለም አቀፍ ዳኞች ከሌሎች አገሮች ጋር ስላላት ጥያቄ ወይም ጉዳይ በተመለከተ የሚሰጧት ግምገማ ወይም ዳኝነት መሰረት ያደረገ ያተረፈችው ነገር እስካሁን ስናየው በጎ በሚባል መልኩ የሚቀመጥ አይደለም።
መንግሥት ‘እውነት ከእኛ ጎን ነች ስለዚህ ያለንን ማስረጃም ይሁን መረጃ ከሰጠን ዓለም ለኛ ይፍረድልናል እናም ማሸነፋችን የማይቀር ነው’ የሚል በሚምስል ምኞት ተመስርቶ ሲሄድ ሂደቶችን ላለማደናቀፍ ስለ ሂደቶቹም፤ ስላቀረባቸው ሰነዶች አይነትና ብዛት እንዲሁም እነማንን እንደዋና ተዋናይ፤ እነማንን እንደ አጋዥ እና አማካሪ እንዳደረገ አይናገርም። ሂደቱ እንዴት እየሄደ እንዳለ በዝርዝርና ሲጀመር ያሉት ልዩነቶች ምን አይነትና ምን ያህል ሚዛን የሚደፉ እንደሆኑ አይገልጽም። ወደማንፈልገው አቅጣጫ እያመራ ከሆነም መዘዙና መውጫ መንገዱ ምን ሊሆን እንደሚችል አይተነትንም - መንግሥት ለህዝቡ።
ከአገሮች ጋር ያለው ከጥቅምና ከደህንነት ጋር የሚተሳሰር ፉክክርና የይገባኛል ጥያቄ በተለይ በዓለም አቀፍ መድረክ በሚታይበት ጊዜ ውስብስብ ነገሮች እንዳሉ ግልጽ ነው። እናም በጥንቃቄና በትእግስት መያዝ ያስፈልገዋል። ጥንቃቄውንና ትእግስቱ ግን ውጤት የማያመጣ እንዲያውም እንደ ድክመት የሚታይ ከሆነ የሚያወጣው ለህዝቡ በግልጽ ስለሂደቶችና ስለጥረቶች መግለጽ ነው - አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ፤  ሲጀምር ብቻ ሳይሆን በመሐልም ሲያልቅም።
እስቲ ወደኋላ ሄደን ሁለት ሂደቶችን እንይ - የባድመና የበራራ 409 ጉዳይ።
አርፈን በተቀመጥንበት ሻዕቢያ ባድመን ሲወርር በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መስዋእትነት ልክ አስገብተን ካስወጣን በኋላ ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሄደ። እነማን ወከሉን?  ምን ምን ማስረጃና መረጃ አቀረቡ? ሂደቱ እንዴት አይነት ቅርጽ እየያዘ ነው? ምን ውጤት እየጠበቅን ነበር? ምንስ እየሆነ ነበር? እነሱስ ምን ምን አይነት ማስረጃ አቀረቡ? ወዘተ መንግሥት ዝርዝር መረጃ አይሰጥም ነበር። እንደ ህዝብ የምናውቀው ነገር አልነበረም። እንዲያውም ባድመ ለእኛ ተፈረደልን በሚል ህዝቡ ደስታውን በአደባባይ እንዲገልጽ ተደርጎም ነበር። ይህ መቼም ትልቅ ስህተት ነው። ከሀ እስከ ፐ ስለሂደቱም ስለይዘቱም ስላቀርብናቸው ሰነዶችም እና ስለሚወክሉን የአገር ውስጥም የውጪም ባለሞያዎች በግልጽነት ማቅረቡ ሲሆን ኧረ ሌላም ማስረጃ አለ፤ እነእገሌም ይካተቱ የሚል ሃሳብ ለመስጠት እና  ውጤቱ የተለየ እንዲሆን የሚያደርግ አስተዋጽኦ ይኖረው ነበር። ባይሆንም እንኳ ቢያንስ መንግሥትና ሕዝብ ‘መቼስ ምን ይደረግ?’ በሚል በአንድ መንፈስ “እግዚሔር ይይላችሁ ዳኞች!” ማለት እንችል ነበር። ይህ አልሆነም።
ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ ከሊባኖስ ተነስቶ አየር ላይ የተቃጠለው አውሮፕላናችን ከነተሳፋሪዎቹ ብትንትኑ ሲወጣ ከሀዘን ጋር ጥያቄዎች መጠየቅ ጀመረን ነበር - እንደዜጋና ህዝብ። ምንድነው የተፈጠረው? ከቁጥጥር ውጪ በሆነ አደጋ  የተከሰተ ነው ወይስ በተመዝግዛጊ ሚሳይል ተመትቶ ነው የተቃጠለው? የማን ጥፋት ነው? እነዚህን እየጠየቅን እያለን እንገደና የእነዚህ መልሶች በዓለም አቀፍ አጣሪ ቡድን እጅ ውስጥ ነው ተብሎ ሂደቱ ተጀመረ። መጨረሻ ላይ በሊባኖስ መንግሥት በኩል ወጣ የተባለው ሪፖርት ልምድ የሌላቸው ፓይለቶች ናቸው ሰላሳ አንድ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ለዘጠና ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው ክስተት መነሻ የሆኑት አሉና አረፉት። ከበረራ ቁጥር 409 ተሳፋሪዎች መካከል የሂዝቦላ ሰዎች የነበሩ ከመሆኑ አኳያ በግሌ ገና ዜናው እንደተሰማ ‘የእስራኤል እጅ ይኖርበት ይሆን? እስራኤል  ማስተላለፍ የምትፈልገው መልእክት ለሌሎች ሆኖ ሳለ አየር መንገዳችንና አገራችን የዛ ማስፈጸሚያ  ጦስ ተደርገው ከሆነስ? ማን ያውቃል?’ በሚሉ ጥያቄዎች ስብከነከን ነበር። በዛ ላይ ፍንዳታ እንደታየና እንደተሰማ ይታወቃል። ምናልባት አጣሪ ኮሚቴው ራሱ አውሮፕላኑ በሚሳይል እንደተመታ ቢደርስበትና የእስራኤልና መሰል አገሮች ስምና ጥቅም ለመጠበቅ ተብሎ የግፍ መስዋእት እንድንሆን ተፈርዶብን ከሆነስ? ማን ያውቃል?  የምናውቀው ግን አሁንም መንግሥት ፍትሀዊ አያያዝ እናገኛለንና መጨረሻውን እንጠብቅ በሚል ዝርዝር ነገሮችን ሳይነግረን አለፈ። ዝርዝር ትንተና የሚጠቅመን የሞቱትን ለመመለስ አይደለም። ምናልባትም ውሳኔውን ለማስቀየርም አይጠቅም ይሆናል። ማወቅ ግን ነበረብን። የፈራነው አልቀረም ዊኪሊክስ የሊባኖስ መንግሥት ሪፖርት ባወጣ ከዘጠኝ ወር በኋላ የእስራኤል ኢራንና ሂዝቦላን ኢላማ በማድረግ ያደረገችው ሊሆን እንደሚችል መረጃ አወጣ።  ሰዎች ለዓለም ስርአት አኳያ የምናስየው ጥንቃቄ አክብሮትና ትእግስት በሌሎች አገርችና ዓለምአቀፍ ተዋናዮች  ዘንድ እንደ ድካም እየተቆጠረ መሄድ የለበትምና መንግሥት ሆይ መናገር አለብህ። ቢያንስ በአገር ውስጥም በውጪም ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን ሳናደርግ ቀረን።
ወደ ታላቁ ግድብ ስንመጣ  አሁንም ዊኪሊክስ ግብጽ ታላቁን ግድብ ባስፈልጋት ጊዜ ከሱዳን ምድር ተነስታ በቀጥታ በጄት ለማውደምም ሆነ በአሻጥር ከጥቅም ውጪ ለማድረግ የሚያስችላት ስራ ለመስራት ከሱዳን ጋር ለመስማማቷ መረጃ አውጥቷል። የመረጃው ምንጭ ደግሞ በሊባኖስ አዎ በሊባኖስ ያሉ የግብጽ አምባሳደር መሆናቸው ቢያንስ አሃ ያሰኛል።
መንግሥት በባለሞያዎቹ ቡድን ውስጥ የተካተቱት ኢትዮጵያዊያን ባለሞያዎችን እነማን እንደሆኑ፤ ምን ልምድና ችሎታ እንዳላቸው፤ እነማን አያማከሩ እንደሆነ መናገር አለበት። መልካማችን መልካማቸው ያልሆኑ ክፍሎች ሊጠቀሙበት የሚችሉ አይነት የማጣሪያ ውጤት ድንገት ‘ከች’ እስኪል መጠበቅ የለብንም።
ሞያ በልብ እንደሆነው ሁሉ ሞያ በግልጽነትም ነው። ምንም ያህል እውነት ከእኛ ጋር ብትሆን የእኛ እውነት የምር በሌሎች ዘንድ ተግባራዊ ተቀባይነት ያገኘ እውነት እንዲሆን ለማድረግ  ጠንካራ ስራ መስራት ካልቻልን ያው ነው። ለህዝብ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ማሳተፍ ያስፈልጋል።
ካለፉት ልምዶቻችን ትምህርት ቀስመን መሄድ አለብን - እንደ አገር። አንድ አይነት ዘዴ በተደጋጋሚ እየተጠቀሙ የተለየ ውጤት መጠበቅ ብልህነት አይደለም።



 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: